በክልሉ በግብይት ወቅት ሕገ ወጥ ተግባር በፈጸሙ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው - የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በግብይት ወቅት ሕገ ወጥ ተግባር በፈጸሙ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው - የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ
አርባ ምንጭ ፤ ሐምሌ 29/2016 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በግብይት ወቅት ሕገ ወጥ ተግባር የፈጸሙ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ገለጸ።
የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ በህገ-ወጥ የንግድ ስርአት ቁጥጥርና ገበያ ማረጋጋት ላይ በተዋረድ ከሚገኙ መዋቅር ሥራ ሃላፊዎች ጋር በአርባ ምንጭ ከተማ ዛሬ ውይይት አድርጓል።
በዚህ ወቅት የቢሮ ሃላፊው አቶ ገሌቦ ጎልሞ እንደገለጹት፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያን ተከትለው በግብይት ወቅት ሕገ ወጥ ተግባር የፈጸሙ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል።
በክልሉ አንዳንድ ነጋዴዎች በግብይት ወቅት ህገ ወጥ ተግባር እንደፈጸሙ ጠቁመው፤ በተለይ ምርቶችን የመደበቅና የማሸሽ ህገ ወጥ ተግባራት መኖራቸውን በተደረገ ምልከታ መረጋገጡን ተናግረዋል።
በክልሉ በየደረጃው የአስተዳደር፣ የፀጥታ፣ የፍትህና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያካተተ የህገ-ወጥ ንግድ ቁጥጥር ግብረ-ሃይል መኖሩንም ጠቁመዋል።
ግብረ-ሃይሉ ባለፉት አምስት ቀናት በ304 የንግድ ድርጅቶች ላይ ባደረገው የክትትልና ቁጥጥር ሥራ በንግድ ልውውጥ ወቅት ሕገወጥ ተግባር ሲፈጽሙ በተገኙ 44 የንግድ ድርጅቶች ላይ ማሸግን ጨምሮ ሌሎች እርምጃዎች መወሰዱን አብራርተዋል።
የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ከህገ ወጥ ድርጊት በመቆጠብ በተጠያቂነት መንፈስ ሥራቸውን ማከናወን ይገባቸዋል ሲሉም አሳስበዋል።