በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ችግር በተለያዩ አማራጮች ለመፍታት እየተሰራ ነው

ሀዋሳ ፤ሐምሌ 29/2016 (ኢዜአ)፦የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ችግር በተለያዩ አማራጮች ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን መምሪያ ለ1 ሺህ 108 የመንግሥት ሠራተኞች ለጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ የሚሆን ቦታ ዛሬ በእጣ አስተላልፏል።

በቦታ ርክክቡ ላይ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መኩሪያ ማርሻዬ እንደገለጹት የቤት ጉዳይ ይበልጥ በከተሞች የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል።

ችግሩን ለማቃለል አስተዳደሩ ለስራው አመቺ የሆኑ መመሪያዎችን በማውጣት ለተግባራዊነቱ በሙሉ ቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት ጥረት እያደረገ ነው ሲሉም ጠቁመዋል።

በተለይ የመንግሥት ሠራተኛውን በቤት ልማት አማራጮች ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፣ በዛሬው እለት ለ1ሺህ 108 የመንግሥት ሠራተኞች የቤት መስሪያ ቦታ ተላልፏል ብለዋል።

መሠረተ ልማት የተሟላለት 51 ሺህ 950 ካሬ ሜትር ቦታ የተላለፈው በመኖሪያ ቤት ሕብረት ሥራ የተደራጁ 35 ማህበራት ለግንባታው ሂደት አስፈላጊውን ገንዘብ በመቆጠባቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

በቀጣይም ሁሉም የከተማዋ ነዋሪ በአቅሙ ልክ ሊሳተፍበት የሚችልበትን የኮንዶሚንየም ቤት አመራጭ  አስተዳደሩ በማዘጋጀት በቅርቡ ምዝገባ እንደሚጀምርም አመልክተዋል።

የሲዳማ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አሻግሬ ጀንበሬ በበኩላቸው ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በክልሉ በከተሞች ለሰው ተኮር ልማት ልዩ ትኩረት በመሰጠቱ የህብረተሰቡ ችግር እየተቃለለ መጥቷል።


 

በክልሉ ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው አንዱ የቤት መስሪያ ቦታ ማመቻቸት መሆኑን ጠቅሰው፣ ቦታውን ያገኙት እድለኞች ደረጃውን የጠበቀ ግንባታ በማካሄድ ለከተማዋ ልማት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ  እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

ቢሮውም የዲዛይን ክትትልና ቁጥጥር ከማድረግ ባለፈ በግንባታ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታት ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ካገኙት መካከል አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ይሁንሰው አብርሃም ቦታ ለማግኘት በማህበር ተደራጅተው በየወሩ ሲቆጥቡ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

አሁን ላይ በከተሞች ያለው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ እየጨመረ መምጣቱ በተለይ ለመንግስት ሠራተኛውና ዝግቀተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች ከአቅም በላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ይህን ችግር አይቶ የቤት መስሪያ ቦታ በመስጠቱ አመስግነው በቅርቡ የቤት ባለቤት የመሆን ተስፋ ሰንቂያለሁ ሲሉ ገልጸዋል።


 

የጤና በለሙያ አቶ ባርናባስ ተስፋዬ በበኩላቸው እሳቸውን ጨምሮ የቤት መስሪያ ቦታ የተሰጣቸው የመንግስት ሠራተኞች ለረጅም ጊዜ በኪራይ ቤት ሲኖሩ እንደነበር አስታውሰዋል። 

የተሰጣቸው የቤት መስሪያ ቦታ ከቤት ኪራይ ወጪ በዘላቂነት ለመገላገል ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል።

ሠራተኞቹ ከተማ አስተዳደሩ አሁን የጀመረው የመኖሪያ ቤት ችግር የመፍታት ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም