የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቻይና-አፍሪካ ትብብርን ይደግፋል - አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30 /2016(ኢዜአ)፡- የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቻይናና አፍሪካ ትብብርና አጋርነትን እንደሚደግፍ የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ገለጹ።

የቻይና-አፍሪካ ጉባኤ ዛሬ በቤጂንግ መካሄድ ጀምሯል።

የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር ላይ ዓለም በግጭቶችና ማህበራዊ ቀውሶች ውስጥ እያለፈች እንደምትገኝና ተግዳሮቶቹ ለእድገትና ልማት ትልቅ ፈተና መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአፍሪካ አገራት በእዳ ቀውስ ፈተና ውስጥ መግባታቸውንና ለዘላቂ ልማት መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ መቸገራቸውን አመልክተዋል።

ኢ-ፍትሐዊና ጊዜው ያለፈበት ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስርዓት ማሻሻያ እንደሚያስፈልገውና የፋይናንስ ተቋማት ፍትሐዊ በሆነ መልኩ የፋይናንስ አቅርቦትን ተደራሽ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በማደግ ላይ የሚገኙ አገራት ፈታኝ የገበያ ሁኔታዎች ተቋቁመው የዘላቂ ልማት ግቦችን እንዲያሳኩ የሚያደርግ የፋይናንስ ድጋፍ ማዕቀፍ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ይህም የአገራትን የፋይናንስ ተደራሽነት በማሳደግ የመካከለኛና የረጅም ዘመን መፍትሔ እንዲያበጁ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።

በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስርዓቱ ፍትሐዊ ማሻሻያ ለማድረግ የአፍሪካና ቻይና ሚና ቁልፍ መሆኑን ነው ዋና ፀሐፊው የገለጹት።

ከዚህ አኳያም የደቡብ-ደቡብ ትብብር የአገራትን አቅም ለመገንባትና የልማት ግቦችን በጋራ እውን ለማድረግ የሚያስችል ማዕቀፍ እንደሆነ ተናግረዋል።

ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላት አጋርነት የደቡብ-ደቡብ ትብብር ዋንኛ ምሰሶ ነው ብለዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቻይና-አፍሪካ ትብብርና አጋርነት እንደሚደግፍ ዋና ፀሐፊው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም