ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት በማደግ ላይ የሚገኙ አገራትን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ እንዲሰሩ  የማሻሻያ ስራዎች ተጀምረዋል - አንቶኒዮ ጉተሬዝ 

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30/2016 (ኢዜአ)፡- የመንግስታቱ ድርጅት ዓለም አቀፍ  የገንዘብ ተቋማት በማደግ ላይ የሚገኙ አገራትን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ እንዲሰሩ የማሻሻያ ስራዎች መጀመሩን የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ50 የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች የታደሙበት የቻይና-አፍሪካ የትብብር ጉባዔ ትናንት በቤጂንግ ተከፍቷል። 

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የቻይናን ያልተቋረጠ ድጋፍ ታደንቃለች ብለዋል።

በጉባኤው ላይ የተገኙት የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ  ከሲጂቲኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ አፍሪካ የቅኝ አገዛዝ ድርብ ተጠቂ መሆኗን ጠቅሰው ጉዳቱ የሚጀምረው ራሱ የቅኝ አገዛዝ ካደረሰባት ጫና መሆኑን አስታውቀዋል።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተቋቋሙ ዓለም አቀፍ ተቋማት ያደረሱባት የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ሌላው ጫና መሆኑን ተናግረዋል።

የቅኝ አገዛዙ ድርብ ጫና በፈጠረባቸው ፈተና በርካታ የአፍሪካ አገራት ህልውናቸውን በራሳቸው አቅም ማስቀጥል የማይችሉ እንደነበሩ ገልጸዋል።

በዚህም አፍሪካ በዓለም አደባባይ በበቂ ሁኔታ መወከል አለመቻሏን በማንሳት ተግባሩን ነጥለን ካየነው በተለይም አህጉሪቱ በኢኮኖሚና በፋይናንስ ዘርፍ የደረሰባት መገለል በጣም አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በማደግ ላይ የሚገኙ አገራትን ፍላጎት በበቂ ሁኔታ ለመሸፈን አለመፈለጋቸውና አገራቱ በተቋማቱ ውስጥ በሚፈለገው ልክ አለመወከላቸው ችግሩን አባብሶታል ብለዋል።

ይሀንን ችግር ለመፍታት የመንግስታቱ ድርጅት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትን አሰራር ለማሻሻል ስራዎች መጀመሩን ጠቅሰዋል።

ማሻሻያው በማደግ ላይ የሚገኙ አገራትን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ እንዲተገበር እየሰራን ነው ብለዋል።

ቻይና ዘላቂነት ያለውን የምዕተ ዓመቱን የልማት ግብ ለማሳካትና የራሷን ጨምሮ በማደግ ላይ ያሉ አገራትን ፍላጎት ለሟሟላት ከፍተኛ ኃላፊነት ወስዳ እየሰራች መሆኑን ዋና ፀሐፊው አስረድተዋል።

የቻይና አፍሪካ ግንኙነት የደቡብ-ደቡብ ትብብርን የሚያንጸባርቅ መሆኑን በመጥቀስ ቻይና አፍሪካ የምትፈልገውን ኢንቨስትመንት በማቅረብ በኩል የሚጠበቅባትን ሚና እየተወጣች መሆኑን ገልጸዋል።

አፍሪካ በመሰረተ ልማት፣ ትምህርትና ጤና ዘርፍ ያሉባትን ጉድለቶች ለመሙላት በምታደርገው ጥረት የቻይና እገዛ ከፍተኛ ቦታ ይይዛል ብለዋል።

ቻይና ለአፍሪካ አገራት እያደረገች ያለው እገዛ ትልቅ እድል ይዞ መምጣቱን የተናገሩት ዋና ፀሐፊው አጀንዳ 2030ን ለማሳካት የቻይና አስተዋጽኦ ከፍተኛ ቦታ እንዳለው ተናግረዋል።

ዘላቂነት ያለውን የምዕተ ዓመቱን የልማት ግብ ለማሳካት ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትን ማሻሻል ዋነኛው እርምጃ መሆኑን አስታውቀዋል።

ለሦስት ቀናት በሚካሔደው የቻይና-አፍሪካ የትብብር ጉባዔ እአአ እስከ 2027 በሚኖረው የቻይና እና አፍሪካ ግንኙነት የትብብር ሰነዶች ላይ ውይይት ተደርጎ ስምምነት እንደሚፈረም ይጠበቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም