አብዱልመጂድ ቴቡኔ በድጋሚ የአልጄሪያ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ - ኢዜአ አማርኛ
አብዱልመጂድ ቴቡኔ በድጋሚ የአልጄሪያ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ
አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 4/2016 (ኢዜአ)፦ አብዱልመጂድ ቴቡኔ የአልጄሪያ ፕሬዝዳንት ሆነው በድጋሚ ተመርጠዋል።
በአልጄሪያ ትናንት በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የ78 ዓመቱ ፖለቲከኛ 95 በመቶ ድምጽ ማግኘታቸውን የአገሪቷ የምርጫ ኮሚሽን አስታውቋል።
አብዴላሊ ሃሳኒ ቼሪፍ 3 በመቶ እና ዩሱፍ ኦውቺቼ 2 በመቶ ድምጽ ማግኘታቸውን ዘ ኢስት አፍሪካን እና አልጀዚራ ኮሚሽኑን ዋቢ አድርገው ያወጡት ዘገባ ያመለክታል።
በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገቡ ከ24 ሚሊዮን በላይ ዜጎች መካከል 48 በመቶው ብቻ ድምጽ መስጠታቸው ተገልጿል።
በምርጫው ላይ ከ800 ሺህ በላይ በተለያዩ አገራት የሚኖሩ የአልጄሪያ ዳያስፖራዎች ድምጽ ሰጥተዋል።
ውጤቱን ተከትሎ አብዱልመጂድ ቴቡኔ ለቀጣይ አምስት ዓመታት አልጄሪያን በመምራት ይቀጥላሉ።
ቴቡኔ ከእ.አ.አ 2019 አንስቶ አልጄሪያን በፕሬዝዳንት እየመሩ እንደሚገኝ የዘ ኢስት አፍሪካን ዘገባ ያመለክታል።