አፍሪካ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት አሜሪካ ዛሬ ድጋፏን ታሳውቃለች - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት አሜሪካ ዛሬ ድጋፏን ታሳውቃለች
አዲስ አበባ፤ መስከረም 2/2017 (ኢዜአ)፡- አፍሪካ በተባበሩት መንግስትት የጸጥታው ምክር ቤት ሁለት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት አሜሪካ ድጋፏን ኒውዮርክ በሚገኘው የድርጅቱ የውጭ ግንኙነት ምክር ቤት ዛሬ እንደምታሳውቅ በድርጅቱ የሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ ገለጹ።
ከአፍሪካ በተጨማሪ አንድ ተዘዋዋሪ መቀመጫ ታዳጊ የደሴት (Highlands) ሀገራት እንዲኖራቸው አሜሪካ እንደምትደግፍ አምባሳደሯ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
አገራቸው አፍሪካ በጸጥታ ምክር ቤቱ ቋሚ መቀመጫዎች እንዲኖራት ድጋፍ ማድረጓ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት በላቀ ሁኔታ እንደሚያሳድገውም አምባሳደሯ ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ሕዝብ ከቢሊዮን በላይ ቢሆንም፣ እ.ኤ.አ. በ1946 የተቋቋመው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ለአኅጉሪቷ ቋሚ መቀመጫ ሳይሰጣት፣ ከ70 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡
ምክር ቤቱ 15 አባላት ያሉት ሲሆን፤ ቋሚ መቀመጫ የሰጠው ግን ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ያላቸው አምስቱ ሀገራት ለአሜሪካ፣ ለቻይና፣ ለፈረንሳይ፣ ለሩሲያና እንግሊዝ መሆኑን ጠቅሶ፣ድርድሮችን ለማበረታታት፣ ማዕቀብ ለመጣል፣ የሰላም አስከባሪ ማሰማራትን ጨምሮ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ለማድረግ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን አለው።
በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ሁሉም የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ ግዛት ነፃ ወጥተው በሂደት ተመድን ቢቀላቀሉም፣ ፀጥታው ምክር ቤት ካሉት አሥር ቋሚ ያልሆኑ መቀመጫዎች ለአፍሪካ የሰጠው ሦስት ተቀያያሪ መቀመጫዎችን እንደሆነም ዘገባው አመልክቷል፡፡
በግጭት የሚታመሱ አገሮች ያሉባት አፍሪካ፣ ድምጿ በቋሚነት እንዲሰማ፣ በሰላምና ፀጥታ ዘርፍ ጉልህ ሚና እንድትጫወት ዛሬ በምክር ቤቱ ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት፣ ለዚህም ተመድ የፀጥታውን ምክር ቤት መልሶ እንዲያዋቅር ስትወተውት ቆይታለች፡፡
እ.ኤ.አ. በ2010 አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት የአኅጉሪቱ መሪዎች ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ ጥያቄያቸው እስካሁን መልስ አላገኘም፡፡
ሰኞ ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም የተመድ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በነበራቸው ውይይትም፣ የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ የፀጥታው ምክር ቤት ያረጀ አወቃቀሩን መልሶ እንዲያዋቅርና አፍሪካን በቋሚ አባልነት እንዲያካትት በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
“ዓለም እየተለዋወጠች ባለችበት ወቅት አፍሪካ የምክር ቤት ቋሚ አባል መሆን አለባት፣ እስካሁን አለመወከሏም ትክክል አይደለም፤” ሲሉ የተናገሩት ጉተሬስ፣ በምክር ቤቱ ያለው ስብጥር አሁን እየተቀየረ ካለው ዓለም ጋር ተመጣጥኖ መሄድ አቅቶታል ብለዋል፡፡
“ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሕዝብ የያዘን አኅጉር በቋሚነት ያላካተተ የሰላምና ፀጥታ አካል አንቀበልም፣ ሰላምና ደኅንነትን በተመለከተ የአፍሪካን አመለካከት ዋጋ የሚያሳጣ አንቀበልም” ሲሉም ለጉባዔው አሳስበዋል፡፡
አፍሪካ ዛሬ በምክር ቤቱ ሁለት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ድጋፏን በአምባሳደሯ በኩል የምታሳውቀው አሜሪካ አፍሪካ በምክር ቤቱ ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ብትደግፍም ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት እንዲኖራት እንደማትፈቅድም ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ መናገራቸውን ዘገባው አመላክቷል።
አፍሪካ በምክር ቤቱ ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት አሜሪካ መደገፏ አፍሪካ በምክር ቤቱ በቋሚነት ትወከል የሚለውን ዘመቻ እንደሚያግዘው አምባሰደሯ አስረድተዋል።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ምክር ቤቱ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ካላቸው ከአምስቱ ቋሚ አገሮች በተጨማሪ አሥር መቀመጫዎችን ለየቀጣናው ቢሰጥም፤ ሀገራቱ ቋሚ መቀመጫ የላቸውም፡፡
በምክር ቤቱ አፍሪካ ሦስት፣ እስያ ፖስፊክ ሁለት፣ ላቲን አሜሪካና ካሪቢያን ሁለት፣ ምዕራብ አውሮፓና ሌሎች ግዛቶች ሁለት እንዲሁም ምሥራቅ አውሮፓ አንድ መቀመጫ እንዳላቸው በመረጃው ተጠቅሷል።