የሴናተር ቦብ ሜኔንዴዝ መጨረሻ - ኢዜአ አማርኛ
የሴናተር ቦብ ሜኔንዴዝ መጨረሻ
በኒው ዮርክ በ12 ዳኞች የተሰየመው ችሎት የ70 ዓመቱ የሕግ ባለሙያ እና ፖለቲከኛ በ16ቱም የሙስና ወንጀሎች ጥፋተኛ ብሏቸዋል።
ለሁለት ወራት የቆየው የክስ ሂደት የሜኔንዴዝን የፖለቲካ ቆይታ እንዲያበቃ ማድረጉን የአሜሪካው የፖለቲካ ዲጂታል ጋዜጣ ፖለቲኮ ዘግቧል።
የአሜሪካ ፌደራል ዐቃቤ ሕጎች የቀድሞውን ሴናተር ጉቦ ተቀብለው የግብጽ ወኪል ሆኖ በመስራት፣ ፍትሕ እንዲዛባ በማድረግ እና የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ወንጀል ከሰዋል።
የአሜሪካ ዐቃቤ ሕግ ሜኔንዴዝ የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ሰብሳቢ በነበሩበት ወቅት የግብጽን ፍላጎት በማንጸባረቅ፣ ለዚህም ከግብጽ መንግስት ገንዘብ ማግኘታቸው በሰነድና በሰው ማስረጃ አረጋግጧል።
የሴናተሩ ባለቤት የሆኑት ናዲኔ ሜኔንዴዝ እ.አ.አ. በማርች 2020 ገደማ ባለቤቷ ሴናተር ሜኔንዴዝ ከአንድ የግብጽ ጦር ጄኔራል ጋር እንዲገናኙ ፕሮግራም ማዘጋጀቷንና በፕሮግራሙ ላይም ሴናተሩ ከግብፅ ጄኔራል ጋር ተገናኝተው በወቅቱ ታላቁ የኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ በግብፅ፣ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ይካሄድ ስለነበረው ድርድር መወያየታቸው የምርመራ መዝገቡ ያመለክታል።
ግብጽ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይን ዋንኛ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዋነኛ የትኩረት ማዕከል አድርጋ ስትሰራበት መቆየቷ መዝገቡ ያሳያል።
ሴናተሩ ከግብፅ ጄኔራል ጋር በተገናኙ በቀጣዩ ወር ውስጥ (በኤፕሪል 2020 ወይም ገደማ)፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ላይ ለሚሳተፉት የአሜሪካ ግምጃ ቤት የቀድሞ ዋና ፀሐፊ ስቴቨን ሙንቺንና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደብዳቤ መጻፋቸውን ይገልጻል።
በደብዳቤው ላይ ኢትዮጵያና ሱዳን በግድቡ ዙሪያ ያደርጉት የነበረው ድርድር መቋረጥ እንዳሳሰባቸው ለመግለጽ ደብዳቤውን መጻፋቸው ተመላክቷል ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በሕዳሴ ግድቡ የሶስትዮሽ ድርድር ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያሳድግ መጠየቃቸውን በምርመራ ሰነዱ ላይ ሰፍሯል።
በ16 የሙስና ወንጀሎች ጥፋተኛ የተባሉት ሜኔንዴዝ የግብፅ መንግስት በሚሊዮን ዶላሮች የሚገመት የአሜሪካ መንግስት ወታደራዊ ድጋፍ እንዲያገኝ ረድተዋል የሚል ክስ እንደቀረባበቸውም የቢቢሲ መረጃ ያመለክታል።
ሜኔንዴዝ የውጪ መንግስታትን ፍላጎት ለማስፈጸም ከተቀበሏቸው ስጦታዎች መካከል 100 ሺህ ዶላር የሚያወጣ ወርቅና ቅንጡ መርሰዲስ መኪና የተጠቀሱ ሲሆን፣ በመኖሪያ ቤታቸውም 480 ሺህ ዶላር ጥሬ ገንዘብ መገኘቱን ጠቁሟል።
የቀድሞው ሴናተር ከግብጽ የንግድ ባለቤቶች ጋር የጥቅም ትስስር እንደነበራቸው ተጠቁሟል።
በክሳቸው ላይ ከግብጽ በተጨማሪ ከሌሎች የውጭ መንግስታት ጉቦ መቀበላቸው በምርምራ እንደተረጋገጠም ተመላክቷል።
ሴናተሩ ጥፋተኛ ከተባሉም በኋላ በሰጡት አስተያየት ሕዝብን በቅንነት ለማገልገል የገባሁትን ቃለ መሐላ አላፈርስኩም ማለታቸው መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
በፍርድ ቤት ክርክር ሂደት ውስጥ የሜኔንዴዝ ጠበቆች ለጥፋቶቹ ሁሉ ተጠያቂ ሚስታቸው ናዲን ናት ሲሉ ይወቅሳሉ። የግል ጥቅሞችን ለማግኘት ጥፋቶቹን ፈጽማለች በማለትም ተከራክረዋል።
ጥፋተኛ በተባሉባቸው ክሶች ምክንያት ከሰኔቱ እንዲሰናበቱ ግፊት በርትቶባቸው የነበሩት ሜኔንዴዝ ከስልጣናቸው መልቀቃቸው ይታወሳል።
ሴናተሩ ጥፋተኛ በተባሉባቸው ወንጀሎች የቅጣት ውሳኔ ከተላለፈባቸው ለበርካታ ዓመታት በእስር ሊቆዩ እንደሚችሉ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በመግለጽ ላይ ናቸው።
በ2025 ለምን ያህል ጊዜ ይታሰራሉ? የሚለው ጉዳይ ምላሽ እንደሚያገኝ ተገልጿል።
ሜኔንዴዝ እ.አ.አ በ2015 በፌደራል የሙስና ወንጀሎች ጥፋተኛ ተብለው የነበረ ቢሆንም ዳኞች የፍርድ ውሳኔ ላይ ባለመድረሳቸው ክሳቸው ውድቅ እንዲሆን መደረጉ የሚታወስ ነው።
እ.አ.አ በ2021 ቶም ማሊኖውስኪ፣ በያንግ ኪም፣ ግሪጎሪ ሚክስ ፣ ዴቪድ ሲሲሊን፣ ብራድ ሼርማንና ማይክል ማካውል ደጋፊነት የተዘጋጀው ‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ኤች አር 6600 ረቂቅ ሕግ መዘጋጀቱ ይታወቃል።
ሕጉ በወቅቱ የኮንግረሱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ተወያይቶበት ለኮንግረሱ መርቶት ነበር።
በወቅቱ የ‘ኤችአር 6600’ ተጓዳኝ ወይም አጋዥ (ኮምፓኒየን ቢል) የሆነው የኢትዮጵያ ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ ፕሮሞሽን አክት ኦፍ 2022’ ወይም ‘ኤስ.3199’ የተዘጋጀው በ70 ዓመቱ ፖለቲከኛና የሕግ ባለሙያ ቦብ ሜኔንዴዝ ዋና አርቃቂነት ነው።
ሕጉ ሴኔቱ እ.አ.አ በ2022 ሊመለከታቸው በጊዜ ሰሌዳው ከያዛቸው ረቂቅ ሕጎች አንዱ ሆኖ እንዲካተት ተወስኖም ነበር።
በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ረቂቅ ሕጎቹ በሕግ አውጪው አካል ድምጽ ተሰጥቶባቸው እንዳይጸድቁ ለማድረግ ሴናተሮችና የኮንግረስ አባላትን በማናገር፣ደብዳቤ በመጻፍ፣ፊርማ በማሰባሰብና በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘመቻ በማድረግ ጥረት አድርገዋል።
ሕጉ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት የሚጎዳና ሉዓላዊነቷን የሚጥስ እንደነበር በተደጋጋሚ ጊዜ ሲገለጽ ቆይቷል።
እነዚህ ሕጎች እንዲፀድቁ ግብጽ ግፊት ስታደርግ እንደነበረም ይታወቃል።
ሴናተሩ ከተከሰሱበት ወንጀል አንዱ ከግብጽ ጉቦ ተቀብለው በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ኢትዮጵያ ጫና እንዲደረግባት ማድረግ ይገኝበታል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት ለመጉዳት እየተንቀሳቀሰች ከምትገኘው ግብጽ በቀጣናው ትርምስ ለመፍጠር እየሰራች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ የባህር በር ለማግኘት ከሶማሊላንድ ጋር ስምምነት መፈራረሟ ይታወቃል።
ይህንንም ተከትሎ ግብጽ አላስፈላጊ የዲፕሎማሲ ትኩሳት ለመፍጠር እና የአገርን ስም የማጠልሸት ተግባር እየፈጸመች ትገኛለች።
ግብጽ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና እያደረገች ያለው ያልተገባ እንቅስቃሴ ቀጣናውን ውጥረት ውስጥ የማስገባት እኩይ ዓላማ ያለው ነው።
ኢትዮጵያ ግብጽ ወደ ቀጣናው የምትልካቸው የጦር መሳሪያዎች እንደ አልሻበብ ያሉ የሽብርተኛ ቡድኖች እጅ ሊወድቁ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳላት በተደጋጋሚ ጊዜ ስትገልጽ ቆይታለች።
ኢትዮጵያ የግብጽን ቀጣናውን የማተራመስ እና ሽብርተኝነትን የመደገፍ አካሄድ የቀጣናውን ሰላም እና መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥል ነው።
ኢትዮጵያም የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ለማተራመስ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በዝምታ እንደማትመለከት አስታውቃለች።
የሶማሊያ መንግሥት ቀጣናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሰራ እንደሚገኝ መንግስት መግለጹ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው የብሔራዊ ደህንነቷን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ሁኔታዎችን ሁሉ በአንክሮ እየተከታተለች ትገኛለች።
ኢትዮጵያን የመጉዳት እና የአባይ ወንዝን እኔ ብቻ በብቸኝነት የመጠቀም አባዜ የተጠናወታት ግብጽ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊያንን ከህዳሴ ግድቡ ግንባታ እና ከልማት ሕልሟ ልታስቆም አልቻለችም።
ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን ፍትሐዊነት እና እኩልነት በተሞላባት እና ዓለም አቀፍ ሕግን ባከበረ መልኩ የመጠቀም አቋምን በተደጋጋሚ ጊዜ ብታወሳውቅም ግብጽ ይሄን ጥሪ ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት ሉዓላዊ አገራት የተፈጥሮ ሀብታቸውን ለዜጎች ጠቀሜታ የማዋል ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ጽንሰ ሀሳብ ተቃርና ቆማለች።
ግብጽ የቅኝ ግዛት ዘመን የትብብር ማዕቀፎችን መሰረት አድርጋ እኔ ብቻ ልጠቀም በሚል ኢ-ሚዛናዊ እሳቤ በውሃ ሀብት የመልማት ጥረቶች እውን እንዳይሆኑ እክል እየፈጠረች ትገኛለች።
ግብጽ ኢትዮጵያ የዜጎቿን ሕይወት ለመቀየር የምታደርጋቸውን ጥረቶች ሙሉ ለሙሉ ውድቅ የሚያደርግ ሀሳብ ማንጸባረቋን በግልጽ ተቃውማ አቋሟን አሳውቃለች።
ግብጽ ጊዜ ያለፈባቸውን የቆዩ ማዕቀፎች ተጠቅማ የናይል ወንዝን እኔ ብቻ ልቆጣጠር የሚለውን ተቀባይነት የሌለው ሀሳብ ትታ ዓለም አቀፍ የሕግ አሰራርና ሁሉን አሸናፊ የሚያደርግ የድርድር አማራጭን እንድትከትል ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ጊዜ ጥሪ ማቅረቧ ይታወቃል።
ግብጽ በቅርቡ ወደ ትግበራ በገባው የናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት በማጽደቅ በቀጣናዊ ልማት እና ትብብር ገንቢና እንድትወጣም ጠይቃለች።
ከተፋሰሱ አገራት ጋር ወደ ሰላማዊ የትብብር አማራጭና ውይይት ዳግም እንድትመልስም አሳስበለች።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በቀጣናው በጋራ የመልማት እና በጋራ የማደግ ፍላጎቷን እውን ለማድረግ የጀመረችን ጥረት አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ተደማጭነት በማስፋት ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ጉልህ ስራዎች መከናወናቸውንና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ አማራጭ የወደብ እና የባህር በር ለማግኘት የጀመረችው ጥረት እንደምትገፋበትም አመልክተዋል።