ከካፋ እና ሸካ ጥቅጥቅ ደኖች እስከ ጨበራ ጩርጩራ ብሄራዊ ፓርክ - ኢዜአ አማርኛ
ከካፋ እና ሸካ ጥቅጥቅ ደኖች እስከ ጨበራ ጩርጩራ ብሄራዊ ፓርክ
ኢትዮጵያ ለምለም ምድር መሆኗን ሁነኛ ማሳያ ከሆኑት መካከል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አንዱ ነው፡፡ ክልሉ በሁሉም አቅጣጫዎች ውብ የተፈጥሮ ፀጋን የተላበሰ ስለመሆኑ በሚያሳዩ አረንጓዴ እጽዋት የተሞላ ነው፡፡
በክልሉ የሚገኙት ካፋ፣ ሸካ፣ ቤንች ሸኮ፣ ዳውሮ፣ ምዕራብ ኦሞ እና ኮንታ ዞኖች አረንጓዴ የለበሱ ድንቅ የተፈጥሮ ጸጋ መገኛዎች ናቸው፡፡ ይህም ክልሉን ትልቅ የቱሪዝም መዳረሻ አድርጎታል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከፍተኛ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራ እንዲሆን ያስቻለው አረንጓዴነቱ(በእጽዋት መሸፈኑ) መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ አረንጓዴ ያስባለው ደግሞ ዓይንን የሚማርኩ እና መንፈስን የሚያድሱ ጥቅጥቅ ያሉ ደኖች በብዛት መኖራቸው ነው፡፡
ለዚህም አብነት ሆኖ የሚነሳው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሳይንስ፣ የትምህርትና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገበው የሸካ ጥብቅና ጥቅጥቅ ደን ነው፡፡ ደኑ(Biosphere) በውስጡ ጫካ፣ የቀርከሃ ዛፎች፣ በውሃ ዙሪያ የሚገኝ ርጥብ መሬት፣ የእርሻ መሬት፣ እንዲሁም የገጠር እና የከተማ ሰፈራ አካባቢዎችን የያዘ ነው፡፡
ከቀዝቃዛ ጀምሮ እጅግ እርጥበታማ የደጋ ስፍራዎች እስከ ሞቃታማ ቆላ ድረስ የአየር ጠባይ የሚስተናገድበትም ነው፡፡ የዩኔስኮ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የሸካ ጥብቅ እና ጥቅጥቅ ደን አጠቃላይ 238ሺህ 750 ሄክታር መሬት ይሸፍናል። የበርካታ እንስሳት እና እጽዋት ዝርያዎች መኖሪያም ነው፡፡
ከ300 በላይ ትላልቅ እጽዋቶች፣ 50 አጥቢ እንስሳት፣ 200 አዕዋፋት እና 20 የእንቁራሪት አስተኔ ዝርያዎች መገኛም ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ብርቅዬና ሀገር በቀል የሆኑ 55 የእጽዋት፣ 10 አዕዋፋት እና 38 የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸው እንስሳትና እጽዋት ዝርያዎች እንደሚገኙም ዩኔስኮ በድረገጹ አስፍሯል፡፡ አረቢካ ቡና፣ ቁጥቋጦ እና ሌሎች የእጽዋት ዝርያዎችም በደኑ ውስጥ ይገኛሉ፡፡
በእንስሳት በኩል በውሃ ውስጥም በየብስም የሚኖሩ፣ ትላልቅና ትናንሽ አጥቢዎች፣ ተሳቢዎች እና የአዕዋፋት ዝርያዎች መኖሪያቸውን በደኑ ውሰጥ አድርገዋል፡፡
ጃርት፣ የተለያዩ የዝንጀሮ ዝርያዎች፣ የአፍሪካ ጎሽ፣ አንበሳ፣ ነብር፣ የአፍሪካ ጥርኝ፣ የኢትዮጵያ ጥንቸል፣ የአቢሲኒያ ባለጥቁርና ቢጫ ቀለም ወፍ እና ግንደ-ቆርቁር ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ዩኔስኮ የሸካ ጥብቅና ጥቅጥቅ ደንን የመዘገበው በአውሮፓውያኑ 2012 ነው፡፡
ከሸካ በተጓዳኝ የካፋ ጥብቅና ጥቅጥቅ ደን(Biosphere) በዩኔስኮ የተመዘገበ ሌላኛው በክልሉ የሚገኝ የቱሪዝም መዳረሻ ነው፡፡ በካፋ ዞን የሚገኘው ደኑ፣ በዓለማችን ተወዳጅ የሆነውውን የአረቢካ ቡና መገናኝ ቦታን ያካልላል፡፡
የብዝሃ- ሕይወት መገኛ የሆነው ደኑ፣ ዩኔስኮ እንደመዘገበው 760 ሺህ 144 ሄክታር መሬት ይሸፍናል። 5 ሺህ የተለያዩ ዓይነት እጽዋቶች መገኛም ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የተለያዩ ዛፎች፣ ቁጥቋጦዎች እና የጫካ ቡና በስፋት ይገኝበታል፡፡
ከእጽዋት ዝርያዎች መካከል 110 የሚሆኑት ሀገር በቀል ናቸው፡፡ አረቢካ ቡና፣ ኮረሪማ፣ የቀርከሃ ዛፎች እና ሌሎችም የእጽዋት ዝርያዎች በስፋት በደኑ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም 300 የሚጠጉ የአጥቢ እንስሳት ዝርያዎች እንዳሉ ይነገራል፡፡
የለሊት ወፍ፣ አይጠ-ሞጎጥ፣ የተለያዩ የዝንጀሮ ዝርያዎች፣ ጉማሬ፣ ጎሽ፣ አጋዘን፣ ጃርት፣ ከርከሮ፣ ጅብ፣ የጫካ አሳማ፣ አንበሳ፣ ነብር፣ ፍልፈል፣ ጥርኝ፣ ቀበሮ እና ጉሬዛ ከእንስሳቱ መካከል ይገኙበታል፡፡
የካፋ ጥብቅ እና ጥቅጥቅ ደን በፈረንጆቹ ሰኔ ወር 2010 ነበር በዩኔስኮ የተመዘገበው፡፡
ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከታደላቸው ሌሎች የተፈጥሮ ሃብቶች መካከል የጨበራ ጩርጩራ ብሄራዊ ፓርክ አንዱ ነው፡፡ ፓርኩ በዳውሮ እና ኮንታ ዞኖች መካከል የሚገኝ ነው፡፡ በአጠቃላይ 1ሺህ 410 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት ይሸፍናል፡፡
ከ1ሺህ 200 እስከ 2ሺህ 300 ሚሊ ሜትር ዓመታዊ የዝናብ መጠን ይመዘገብበታል፡፡ ሙቀት ደግሞ ከ10 ድግሪ ሴልሺየስ እስከ 29 ድግሪ ሴልሺየስ። ከመጋቢት እስከ መስከረም ወራት ድረስ እርጥበታማ ወቅቶች ሲሆኑ፣ ከታህሳስ እስከ የካቲት ደግሞ ፓርኩ ደረቅ ወቅቶችን ያስተናግዳል፡፡
ፓርኩ ትናንሽ ሃይቆች በውስጡ ሲይዝ፣ ቡሎ፣ ከበሪላ፣ ሽታ እና ጮፎሬ ሃይቆች አብነት ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡ በርካታ ወንዞችንም እንዲሁ በውስጡ ይዟል፡፡ ወደ 49 የሚጠጉ ወንዞች ከፓርኩ በመነሳት ወደ ኦሞ ወንዝ ይገባሉ፡፡ የአሳ ዝርያዎች፣ ፍል ውሃዎች፣ ፏፏቴዎች እና ዋሻዎችን የተቸረ ውብ የተፈጥሮ ፀጋ ባለቤት ነው፡፡
በተጨማሪም 37 ዓይነት ትላልቅ አጥቢ እንስሳት እና 237 የአዕዋፋት ዝርያዎች መገኛም ነው። ከአጥቢ እንስሳት መካከል የአፍሪካ ዝሆኖች፣ ጉማሬ፣ ጎሽ፣ አንበሳ፣ ነብር፣ አምባራይሌ፣ የተለያዩ የዝንጀሮ ዝርያዎች እና ከርከሮ ይገኙበታል፡፡
ጨበራ ጩርጩራ ብሄራዊ ፓርክ በ1997 ዓ.ም በብሄራዊ ፓርክነት እንደ ተቋቋመ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ፓርኩ የብዝሃ-ሕይወት እና የአስደማሚ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት በመሆኑ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎች ዋነኛው ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡