አቪዬሽን የኢትዮጵያና ፈረንሳይ ወዳጅነት ማሳያ - ኢዜአ አማርኛ
አቪዬሽን የኢትዮጵያና ፈረንሳይ ወዳጅነት ማሳያ
በመቶ ዓመታት የሚቆጠረው የኢትዮጵያና ፈረንሳይ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ እኤአ በ1907 ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ ፈረንሳይ ኤምባሲዋን በኢትዮጵያ እንድትከፍት አስችሏል።
ከዚህ በኋላም በብዙ መስኮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው እያደገና እየጎለበተ መጥቶ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በትምህርት፣ በሰላምና ጸጥታ የጠበቀ ትስስር መፍጠር አስችሏቸዋል።
ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ በአቪዬሽን ዘርፍም ያላቸው ትብብር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል።
ሁለቱ ሀገራት በ2009 ዓ.ም በሲቪል አቪዬሽን፣ በአየር ትራንስፖርት እና መሰረተ ልማት ዘርፎች ትብብራቸውን ማጠናከር የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል።
በ2008 ዓ.ም ተመሳሳይ ስምምነት አካሂደው የነበረ ሲሆን 2009 ዓ.ም ያደረጉት ስምምነት ከወቅቱ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ፍላጎት ጋር እንዲጣጣም በማድረግ በድጋሚ ተሻሽሎ እንደተፈረመ በወቅቱ ተገልጿል።
ስምምነቱ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፈረንሳይ የሚያደርገውን ሳምንታዊ በረራ የሚያሳድግ እና በቀጣይም ተጨማሪ በረራዎችን ለማድረግ የሚያስችል ነው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን ኤር ባስ ኤ350-1000 "Ethiopia land of origins" የተሰኘ የመንገደኞች አውሮፕላን ከፈረንሳዩ የኤር ባስ ኩባንያ በጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም መረከቡ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዚህ ቀደም የኤ350-900 አውሮፕላኖችን ጨምሮ ሌሎች በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆኑ አውሮፕላኖችን ቀድሞ በማስገባት የሚታወቅ ነው።
ኢትዮጵያ ኤ350-1000 የኤር ባስ አውሮፕላን የተረከበች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ሀገር መሆኗ ካለው ታሪካዊ ስኬት ጎን ለጎን ሁለቱ ሀገራት በአቪዬሽን ዘርፍ ያላቸው ትብብር እያደረገ መምጣቱን የሚያመላክትም ነው።