ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ ይበልጥ የተጠናከረው የኢትዮጵያና ፈረንሳይ ወዳጅነት - ኢዜአ አማርኛ
ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ ይበልጥ የተጠናከረው የኢትዮጵያና ፈረንሳይ ወዳጅነት
የኢትዮጵያና ፈረንሳይ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ዘመናትን የተሻገረ ቢሆም በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ በብዙ ዘርፎች ግንኙነቱ ይበልጥ ጎልብቷል።
በዚህም በሀገራቱ መካከል በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በትምህርት፣ በሰላምና ጸጥታ፣ በአቪዬሽንና በሌሎችም መስኮች የጠበቀ ትስስር መፍጠር ተችሏል።
የሀገራቱ ትብብር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመሪዎች የጉብኝት ልውውጦች እና የሁለትዮሽ ውይይቶች ይበልጥ እየጠነከረ መጥቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም በአውሮፓ ሀገራት የስራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት አንደኛዋ መዳረሻቸው ፈረንሳይ ነበረች።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ከፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ሁለቱ ሀገራት በትብብር በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ይታወቃል።
ከእነዚህ መካከልም በዓለም አቀፍ መድረክ አንድ በሚያደርጓቸው አጀንዳዎች፣ በጸረ ሽብርና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ፈረንሳይን ከጎበኙ ከአምስት ወራት በኋላ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት አድርገዋል።
ፕሬዚደንት ማክሮን ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ሁለቱ ሀገራት በተለያዩ መስኮች መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነቶች ተፈራርመዋል።
ከስምምነቶቹ መካከል ፈረንሳይ ለላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ቅርስ እድሳት የሙያና የገንዘብ ድጋፍ የምታደርግበት ማዕቀፍ ይጠቀሳል።
ፕሬዚደንት ማክሮን በወቅቱ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን መጎበኝታቸው የሚታወስ ነው።
ኢንቨስትመንት እና መከላከያ ሌሎቹ ስምምነት የተፈረመባቸው መስኮች ናቸው።
የሁለቱ መሪዎች የጉብኝት ልውውጦች የኢትዮጵያ እና የፈረንሳይን ትብብር በማጠናከር ረገድ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከአራት ዓመታት በኋላ በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም በፈረንሳይ የስራ ጉብኝት አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር የሁለቱን ሀገራት የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸው ይታወሳል።
በርካታ የፈረንሳይ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በመሰማራት በሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሥራ እድል መፍጠራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ኢትዮጵያ የግብርና ምርቶችን በተለይም ቡና ወደ ፈረንሳይ ስትልክ ፈረንሳይ የትራንስፖርት ቁሳቁሶችና የህክምና መገልገያ መሳሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ በዋናነት ትልካለች።
በአሁኑ ወቅት ሁለቱ ሀገሮች በመካከላቸው ያለው የኢኮኖሚ ትስስር እየጎለበተ መጥቷል።
የፈረንሳይ የአውሮፓ እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂያን ኖኤል ባሮት በሕዳር 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት ጠንካራ ግንኙነት ይበልጥ ማጎልበትን አላማ ያደረገ ነበር።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋር የሀገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።
ባሮት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ጋርም በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ይታወሳል።
ሚኒስትር ጂያን ኖኤል ባሮት በቆይታቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየምንና በፈረንሳይ መንግሥት የተመሠረተውን የሊሴ ገብረ ማርያም ትምህርት ቤት ጎብኝተዋል።
ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ1960ዎቹ ከመልካ ቁንጥሬ መካነ ቅርስ ለምርምር ወደ ፈረንሳይ ተወስደው የነበሩ ጥንታዊ የሰው ዘር የተገለገለባቸውን የድንጋይ መሣሪያዎች ለቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ማስረከባቸውም እንዲሁ።
በወቅቱ በፈረንሳይ መንግሥት በኢትዮጵያ የሚተገበር ቀጣይነት ያለው የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ፕሮጀክት ይፋ ተደርጓል።
ፕሮጀክቱ በ2011 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያናትና የብሔራዊ ሙዚየም እድሳትን አስመልክቶ ስምምነት የደረሱበት ስራ አካል ነው።
በሚኒስትሩ ጉብኝት ወቅት የትምህርት ሚኒስቴር ከፈረንሳይ ጋር በዘርፉ ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል።
ስምምነቱ ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ የተለያዩ ነጻ የትምህርት እድሎችን ለመስጠት፣ እንዲሁም በሊሴ ገብረማሪያም ትምህርት ቤት የስኮላር ሺፕ መርሃ ግብሮችን ለማጠናከር የሚያስችል ነው።
ባሮት የአፍሪካ ሕብረት ዋና መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ ሕብረት እና ፈረንሳይ የከፍተኛ ደረጃ ስትራቴጂካዊ ምክክር መድረክ ላይም ተሳትፎ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ የፈረንሳይ ኩባንያዎች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እያደረጉ ያሉትን ተሳትፎ በማጠናከር የሁለቱ ሀገራት የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትብብር እንዲያድግ ፍላጎት አላት።
ሁለቱ ሀገራት የጋራ ፍላጎታቸው በሆኑ የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን የትብብር ጉዳዮች ላይ ያላቸው ትስስር እንዲያድግም ትሻለች።
ፈረንሳይም የኢትዮጵያን ሀገራዊ ምክክር ሂደት እና የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ትግበራን ጨምሮ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች።
ኢትዮጵያ እያከናወነች ላለችው ፈጣን የልማት እንቅስቃሴ ፈረንሳይ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልም እንዲሁ።
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በድጋሚ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ መምጣትም ይሄንኑ ከፍታ የሚያሳይ ነው።
ጉብኝቱ የሀገራቱን ጠንካራ ወዳጅነት ይበልጥ የማጽናት ፍላጎት አካል ነው ተብሎ ሊወሰድም ይችላል።