ዘመን ተሻጋሪው የኢትዮጵያ እና የፈረንሳይ ወዳጅነት - ኢዜአ አማርኛ
ዘመን ተሻጋሪው የኢትዮጵያ እና የፈረንሳይ ወዳጅነት
ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ረዥም ዘመን ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ሲሆኑ ግንኙነታቸው ከ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት እንደተጀመረ የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ።
የሀገራቱ ግንኙነት እየተጠናከረ ሲመጣ የወዳጅነትና የንግድ ስምምነት ወደ ማድረግ እንደተሸጋገሩና በተለይ ኢትዮጵያ የአድዋ ድልን ከተቀዳጀች በኋላ እኤአ በየካቲት ወር 1897 የኢትዮ-ጂቡቲ የድንበር ስምምነት በመፈራረም የዲፕሎማሲያዊ ትብብራቸውን መሰረት ጥለዋል።
እኤአ በ1904 የኢትዮጵያና የፈረንሳይ የወዳጅነት ቢሮ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ መከፈቱ ለግንኙነታቸው መጠናከር የበኩሉን ሚና ተጫውቷል።
ግንኙነታቸው የበለጠ ተጠናክሮ እኤአ በ1907 ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ ኤምባሲዋን በኢትዮጵያ ከፍታለች።
ከዚያ በኋላ እ.ኤ.አ በ1943 የኢትዮጵያና የፈረንሳይ የባህል ትብብር ማዕከል፣ በ1947 ሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤትን፣ በ1955 የፈረንሳይ አርኪኦሎጂ ሚሽንን ወደ የፈረንሳይ ኢትዮጵያ የጥናት ማዕከል እንዲያድግ ማድረግና የሁለትዮሽ ግንኙነቱ በሁሉም መስክ እንዲጠናከር ተደርጓል።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላም የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ጀነራል ጉሌ በኢትዮጵያ ጉብኝት ሲያደርጉ፤ በ1973 ደግሞ ሌላው የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጅ ፖምፒዱ ያደረጉት ጉብኝት ግንኙነቱ ወደ ላቀ ደረጃ መሸጋገሩን የሚያመላክት ነበር።
ሁለቱ ሀገራት የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን 125ኛ ዓመት ክብረ በዓል በ2014 ዓ.ም በተለያዩ መርኃ ግብሮች አክብረዋል።
ከሁነቶቹ መካከል በአዲስ አበባ የሁለቱን ሀገራት የንግድ ግንኙነት ማጠናከርን አላማ በማድረግ የተካሄደው የኢንቨስትመንት ፎረም ይገኝበታል።
በፎረሙ ላይ የኢትዮጵያ እና የፈረንሳይ ኩባንያዎች ተሳትፈዋል።
የ125ኛ ዓመት ሁነቱ የግንኙነት ዓመታቱን ከመዘከር ባለፈ ሀገራቱ ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ዳግም ቃል ኪዳናቸውን ያደሱበት ሆኗል።
ግንኙነቱ መንግሥታዊ ብቻ ሳይሆን ጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርንም ያካተተ ነው።
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች የጉብኝት ልውጦች
የሀገራቱ ትብብር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጉብኝት ልውውጦች እና የሁለትዮሽ ውይይቶች ይበልጥ እየጠነከረ መጥቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም በአውሮፓ ሀገራት የስራ ጉብኝት ሲያደርጉ አንደኛዋ መዳረሻቸው ፈረንሳይ ነበረች።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ከፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ሁለቱ ሀገራት በትብብር በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ይታወቃል።
ከእነዚህም መካከል በዓለም አቀፍ መድረክ አንድ በሚያደርጓቸው አጀንዳዎች፣ በጸረ ሸብርና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውም እንዲሁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ፈረንሳይን ከጎበኙ ከአምስት ወራት በኋላ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸውም የሚታወስ ነው።
ማክሮን ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ሁለቱ ሀገራት በተለያዩ መስኮች በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነቶች ተፈራርመዋል።
ከስምምነቶቹ መካከል ፈረንሳይ ለላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ቅርስ እድሳት የሙያና የገንዘብ ድጋፍ የምታደርግበት ማዕቀፍ ይጠቀሳል።
ማክሮን በወቅቱ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን መጎበኝታቸው የሚታወስ ነው።
ኢንቨስትመንት እና መከላከያ ሌሎቹ ስምምነት የተፈረመባቸው መስኮች ናቸው።
የሁለቱ መሪዎች የጉብኝት ልውውጦች የኢትዮጵያ እና የፈረንሳይን ትብብር በማጠናከር ረገድ ወሳኝ ሚና የተጫወተ ነው ማለት ይቻላል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከአራት ዓመታት በኋላ በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም በፈረንሳይ የስራ ጉብኝት አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር የሁለቱን ሀገራት የንግድ እና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።
በርካታ የፈረንሳይ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በመሰማራት በሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሥራ እድል መፍጠራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ኢትዮጵያ የግብርና ምርቶችን በተለይም ቡና ወደ ፈረንሳይ ስትልክ ፈረንሳይ በበኩሏ የትራንስፖርት ቁሳቁሶችና የህክምና መገልገያ መሳሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ በዋናነት ትልካለች።
በአሁኑ ወቅት ሁለቱ ሀገሮች በመካከላቸው ያለው የኢኮኖሚ ትስስር እየጎለበተ መጥቷል።
የፈረንሳይ የአውሮፓ እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂያን ኖኤል ባሮት በሕዳር 2017 ዓ.ም የሁለቱን ሀገራት ጠንካራ ግንኙነት ይበልጥ ማጎልበትን አላማ ያደረገ የስራ ጉብኝት በኢትዮጵያ አድርገው ነበር።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋር የሀገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸው ይታወሳል።
ሚኒስትሩ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ጋርም በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየምንና በፈረንሳይ መንግሥት የተመሠረተውን የሊሴ ገብረ ማርያም ትምህርት ቤት መጎብኘታቸውም እንዲሁ።
ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ1960ዎቹ ከመልካ ቁንጥሬ መካነ ቅርስ ለምርምር ወደ ፈረንሳይ ተወስደው የነበሩ ጥንታዊ የሰው ዘር የተገለገለባቸውን የድንጋይ መሣሪያዎች ለቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ማስረከባቸው ይታወሳል።
በወቅቱ በፈረንሳይ መንግሥት በኢትዮጵያ የሚተገበር ቀጣይነት ያለው የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ፕሮጀክት ይፋ የተደረገ ሲሆን ፕሮጀክቱ በ2011 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያናትና የብሔራዊ ሙዚየም እድሳትን አስመልክቶ ስምምነት የደረሱበት ስራ አካል ነው።
በሚኒስትሩ ጉብኝት ወቅት የትምህርት ሚኒስቴር ከፈረንሳይ ጋር በዘርፉ ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል።
ስምምነቱ ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ የተለያዩ ነጻ የትምህርት እድሎችን ለመስጠት፣ እንዲሁም በሊሴ ገብረማሪያም ትምህርት ቤት የስኮላር ሺፕ መርሃ ግብሮችን ለማጠናከር የሚያስችል ነው።
ባሮት የአፍሪካ ሕብረት ዋና መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ ሕብረት እና ፈረንሳይ የከፍተኛ ደረጃ ስትራቴጂካዊ ምክክር መድረክ ላይም ተሳትፎ አድርገዋል።
አቪዬሽን ሌላኛው የአገራቱ የወዳጅነት ማጋመጃ ዘርፍ
ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ በአቪዬሽን ዘርፍ ያላቸው ትብብርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል።
ሁለቱ አገራት በ2009 ዓ.ም በሲቪል አቪዬሽን፣ በአየር ትራንስፖርት እና መሰረተ ልማት ዘርፎች ትብብራቸውን ለማጠናከር የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል።
በ2008 ዓ.ም ተመሳሳይ ስምምነት አካሂደው የነበረ ሲሆን የ2009 ዓ.ም ያደረጉት ስምምነት ከወቅቱ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ፍላጎት ጋር እንዲጣጣም በማድረግ በድጋሚ ተሻሽሎ እንደተፈረመ በወቅቱ ተገልጿል።
ስምምነቱ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፈረንሳይ የሚያደርገውን ሳምንታዊ በረራ የሚያሳድግ እና በቀጣይም ተጨማሪ በረራዎችን ለማድረግ የሚያስችል ነው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን ኤር ባስ ኤ350-1000 "Ethiopia land of origins" የተሰኘ የመንገደኞች አውሮፕላን ከፈረንሳዩ የኤር ባስ ኩባንያ በጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም መረከቡ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዚህ ቀደም የኤ350-900 አውሮፕላኖችን ጨምሮ ሌሎች በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆኑ አውሮፕላኖችን ቀድሞ በማስገባት የሚታወቅ ነው።
ኢትዮጵያ ኤ350-1000 የኤር ባስ አውሮፕላን የተረከበች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት አገር መሆኗ ካለው ታሪካዊ ስኬት ጎን ለጎን ሁለቱ አገራት በአቪዬሽን ዘርፍ ያላቸው ትብብር እያደረገ መምጣቱን የሚያመላክትም ነው።
በአገራቱ መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ከፍ የማድረግ መሻት አለ።
ኢትዮጵያ የፈረንሳይ ኩባንያዎች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እያደረጉ ያሉትን ተሳትፎ በማጠናከር የሁለቱ አገራት የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትብብር እንዲያድግ ፍላጎት አላት።
ሁለቱ አገራት የጋራ ፍላጎታቸው በሆኑ የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን የትብብር ጉዳዮች ላይ ያላቸው ትስስር እንዲያድግም ትሻለች።
ፈረንሳይም የኢትዮጵያን አገራዊ ምክክር ሂደት እና የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ትግበራን ጨምሮ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች።
ኢትዮጵያ እያከናወነች ላለችው ፈጣን የልማት እንቅስዋሴ ፈረንሳይ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልም እንዲሁ።
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ይፋዊ የስራ ጉብኝትም ይሄንኑ ከፍታ የሚያሳይ ይሆናል።
ጉብኝቱ የአገራቱን ጠንካራ ወዳጅነት ይበልጥ የማጽናት ፍላጎት አካል ነው ተብሎ ሊወሰድም ይችላል።