በአፍሪካ ህብረት ጉባዔ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለመገንባት ዝግጅት አድርገናል -በጎ ፍቃደኞች - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ህብረት ጉባዔ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለመገንባት ዝግጅት አድርገናል -በጎ ፍቃደኞች
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 13/2017(ኢዜአ)፦በ38ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባዔ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለመገንባት ዝግጁ መሆናቸውን በጎ ፍቃደኞች ገለጹ።
ኢትዮጵያ 38ኛውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በሰለጠነ የሰው ኃይል በመታገዝ በብቃት ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት ማድረጓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ የህብረቱ መቀመጫና የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ በሁሉም መስክ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቋም ተገልጿል።
በጉባኤው ላይ የሚሳተፉ እንግዶችን ለማስተናገድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዕጩና ነባር ዲፕሎማቶች እንዲሁም ለበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል።
የስልጠናው ተሳታፊዎች በአዲስ አበባ እየተገነባ ያለውን የአዲስ ዓለም አቀፍ የኮንቬንሽንና ኤግዚቢሽን ማዕከል እንዲሁም የኮሪደር ልማት ስራዎችንና የተለያዩ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን ጎብኝተዋል።
በጎ ፍቃደኛ ወጣት ምርትነሽ ካሳሁን ለኢዜአ በሰጠችው አስተያየት በ38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ እድል በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ ብላለች።
በኢትዮጵያ የተፈጠረው ሠላምና መረጋጋት እንዲሁም ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለገጽታ ግንባታው ትልቅ ሚና እንዳለው ተናግራለች።
በጎ ፍቃደኛ ወጣት ባቻክ ኡጁሉ በበኩሉ በጉብኝቱ የተመለከተው የልማት እና የመሰረተ ልማት ዝርጋታ የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ነው ያስታወቀው።
ያገኘሁት ዕድል ለአገሬ የሚጠበቅብኝን አስተዋጽኦ ለማበርከት መልካም አጋጣሚ ፈጥሮልኛል ብሏል፡፡
ከስልጠናው ባገኘሁት ዕውቀት በመታገዝ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ በሚጠበቀው ደረጃ ለማስተዋወቅ ቁርጠኛ ነኝ ሲልም አክሏል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኮንፍረንስ፣ ሁነትና የመንግሥት ፕሮቶኮል ዳይሬክተር እሸቱ ለገሰ በበኩላቸው፥ በአፍሪካ ህብረት ጉባዔ ላይ የሚሳተፉ እንግዶች ኢትዮጵያ የደረሰችበትን ደረጃ እንዲገነዘቡ የሚያስችል አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራ መከናወኑን አስታውቀዋል።
በተለያዩ ቋንቋዎች የኢትዮጵያን ገጽታ የሚያስተዋውቁ በጎ ፍቃደኞች ስልጠና በመውሰድ ላይ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
ዛሬ የተደረገው ጉብኝት ሰልጣኞች በቂ ግንዛቤ ጨብጠው አገራቸውን እንዲያስተዋውቁ ያለመ መሆኑን ነው የገለጹት።
የውጭ ጉዳይ ኢኒስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር በረከት ድሪባ በ38ኛው የህብረቱ ጉባኤ የሚሳተፉ እንግዶች የኢትዮጵያን ገጽታ በላቀ ደረጃ እንዲረዱ በቂ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።
በጎ ፍቃደኞቹ የውጭ ጉዳይ ዲፕሎማሲን ጨምሮ እንግዶችን ተቀብሎ በማስተናገድ ረገድ ልምድ ባላቸው አሰልጣኞች ግንዛቤ እንዲጨብጡ በመደረግ ላይ መሆኑን ነው ያስታወቁት።
ኢትዮጵያ ከኮንፍረንስ ቱሪዝም ይበልጥ እንድትጠቀም የሰለጠነ የሰው ኃይል ወሳኝ በመሆኑ መሰል ስልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።