ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ተሸፍኗል- ሚኒስቴሩ

ደሴ፤ ታኅሣሥ 15/2017 (ኢዜአ)፦ በአገር አቀፍ ደረጃ ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት መሸፈኑን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን(ዶ/ር)ን ጨምሮ ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ተጀምሯል።

ሚኒስትር ዴኤታው በዚሁ ወቅት እንዳሉት የበጋ መስኖ ስንዴ ምርታማነትን በማሳደግ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ምርት በስፋት ለገበያ ለማቅረብ እየተሰራ ነው፡፡

የውሃ አማራጮችን በመጠቀም ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ትኩረት መስጠቱን ጠቁመው፤ በዘንድሮው የበጋ ወራት ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በስንዴ ለማልማት እየተሰራ ይገኛል፡፡

እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴም ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር የሚበልጥ መሬት በስንዴ ዘር መሸፈን እንደተቻለ ነው የተናገሩት።

ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዙ ማዳበሪያን ጨምሮ ሌሎች ግብዓቶችን በበቂ መጠን እያቀረበ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል ገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪና ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም 254 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ በማልማት ከ9 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልፀዋል፡፡

እስካሁን ከ120 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በዘር መሸፈኑን ጠቁመዋል።

በክልሉ በተሻሻለ አሰራር ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ በቂ ምርት ለገበያ እንዲቀርብ ጭምር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም