የኃይል ልማት ለቀጣናዊ ትስስር - ኢዜአ አማርኛ
የኃይል ልማት ለቀጣናዊ ትስስር
ወዳጅ ማብዛትና አጋር ማበራከት የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መርህ ነው። ፖሊሲዋ ለጎረቤት አገራት ቅድሚያና ልዩ ትኩረት ይሰጣል። ለቀጣናዊ ትስስር፣ የጋራ እድገትና ተጠቃሚነት ትኩረት የዲፕሎማሲዋ አስኳል ነው።
ቀጣናዊ ትስስሩን ዕውን ለማድረግ ከፊት ተሰላፊ ሀገር ናት። በዚህም በትብብር ዲፕሎማሲና የህዝብ ለህዝብ ትስስርን በማጎልበት የጋራ ልማትን ማረጋገጥ ሰርክ ታነሳለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የኢትዮጵያ የሁልጊዜም ፍላጎት በቀጣናዊ ትብብር ከጎረቤት አገራት ሰላም እንዲመጣ በትብብር መሥራት፣ አብሮ ማደግና በጋራ መበልጸግ መሆኑንም በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይደመጣል። ከቀጣናው ሀገራት ትብብር መስኮች አንዱ በኃይል መሰረተ ልማት መተሳሰር መሆኑ እሙን ነው።
ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ የውሃ ማማ መባሏ በምክንያት ነው። ከወንዞቿ በዓመት 124 ቢሊዮን ኪዩብ ሜትር እንዲሁም ከከርሰ ምድር ከ36 እስከ 40 ቢሊዮን ኪዩብ ሜትር ውሃ ሀብት እንዳላት መረጃዎች ያሳያሉ። ይህ የውሃ ሀብቷ ደግሞ ታዳሽ ኃይል ግንባታ አይተኬ ሚና አለው። የውሃ ሀብቷ ከፀሐይ፣ በነፋስ እና በጂኦ-ተርማል የኃይል አማራጮች ጋር ተዳምሮ ከ300 እስከ 400 ጊጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም አላት።
በ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅዷ ኢትዮጵያ የምታመነጨውን የኃይል መጠን አሁን ካለበት 4 ሺህ 818 ሜጋ ዋት ወደ 17 ሺህ ሜጋ ዋት ለማሳደግ ግብ ተቀምጧል። የተሻሻለው የኢነርጂ ፖሊሲዋም ሀገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፍ ነባራዊ ዕውነታ መሰረት ያደረገ እና ጎረቤት ሀገራትን በኃይል መሰረተ ልማት ለማስተሳሰር ያለመ ነው።
በ10 ዓመት መሪ ዕቅዱ መሰረት ለጎረቤት አገራት እየቀረበ ያለውን 2 ሺህ 803 ጊጋ ዋት ሰዓት ሽያጭ ወደ 7 ሺህ 184 ጊጋ ዋት ሰዓት ለማሳደግ ውጥን ተይዟል።
ኢትዮጵያ በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ለጅቡቲ በ2011፣ ለሱዳን በ2012፣ ለኬንያ በ2022 እንድሁም በቅርብ ጊዜ ለታንዛኒያ ኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ ጀምራለች። የኃይል ሽያጩ በየዓመቱ እያደገ መጥቶ በ2015 በጀት ዓመት ወደ 101 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር እንዳደገ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ ያመለክታል።
የቀጣናው ከፍተኛ ኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ (ሃይዌይ) ፕሮጀክት የመጀመሪያው ምዕራፍ ኢትዮጵያና ኬንያን፤ በቅርብ ወደ አገልግሎት የገባው ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ኬንያንና ታንዛኒያ አስተሳስሯል። የኃይል አቅርቦቱ ከሶስቱ ሀገራት ባሻገር ለቀጣናው ሌሎች ሀገራትም ትስስር መሰረት ጥሏል።
ኢትዮጵያ በቀጣይ ለደቡብ ሱዳን፣ ሩዋንዳ፣ ብሩንዲና ሌሎች አገራት የኤሌክትሪክ ኃይል የመሸጥ ዕቅድ ይዛለች። ወደ ደቡብ ሱዳን የሚደረገው ኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ በሂደት ላይ መሆኑ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ ቀጣናውን በኃይል አቅርቦት ረገድ የጋራ ልማትን መሰረት ያደረገ በመሆኑ በተመጣጣኝ ዋጋ ነው የምታቀርበው። ሀገራቱ ከኢትዮጵያ የሚገዙት የኃይል አቅርቦት ደግሞ ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፋቸው እመርታ ፈጥሯል።
ይህ ደግሞ ወዲህ የጎረቤት ሀገራትን ቅድሚያ የሰጠውን ፖሊሲዋን በተግበር የገለጠ ነው፤ ወዲያ ደግሞ ከውጭ ምንዛሬ ግኝት ባሻገር ለቀጣናዊ ትስስርን ለማጎልበት አይተኬ ሚና ይኖረዋል። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት እንዲሁም ለአፍሪካ አጀንዳ 2063 ዕውን መሆን በኢነርጂ ዘርፍ ያላትን ቀዳሚ ስፍራ ያረጋገጣል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ ትስስር ሌላው በረከት ነው። ግንባታው በመጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ የሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ገጸ ብዙ ፕሮጀክት ነው። ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ ልዩ በረከት ይዞ የመጣ፤ የታዳሽ ኃይል ልማት አብነት ነው።
በዐባይ ወንዝ የዘመናትን ብክነትና ቁጭት የቋጨ ነው። በሌላ ጎኑ በራስ አቅም ብቻ የተጠናቀቀ ነው። በአፍሪካ ግዙፉ የኃይል ማመንጫ ግድብና ለቀጣናው ሀገራት ትስስር መልህቅ ስለሆነም ፓን አፍሪካዊ ፕሮጀክት ያሰኘዋል።
ኃይል ማመንጨት የጀመረው ግድቡ በዓመት 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል። እስካሁን በግድቡ አራት ተርባይኖች ኃይል እያመነጩ ነው። ግድቡ ተጠናቆ የሁሉም ተርባይኖች ስራ ተጠናቆ ወደ ምርት ሲገባ ሀገራዊ የኃይል አቅምን 130 በመቶ ያሳድጋል።
ይህ ደግሞ አንድምታም ብዙ ነው። ሀገራዊ የኃይል ፍላጎትን ከመሸፈን አልፎ በቀጣነው ሀገራት ተደራሽ በመሆን የኢትዮጵያን አፍሪካን የማስተሳሰር ቀንዲልነት ያጎላል። ለዚህ ነው ግድቡ ለቀጣናው ሀገራት ገጸ በረከት ነው የሚያሰኘው። በርግጥ ከሕዳሴው ግድብ ባሻገር ሌላው ከአፍሪካ ግዙፍ ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነው የኮይሻ ኃይል ማመንጫም ለቀጣናዊ ትስስር መፋጠን ሌላው እድል ነው።
በጥቅሉ ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት የምታቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይል የሀገራት ኢኮኖሚ ትብብር የሚያጠናክር እና የኢትዮጵያን የመሰረተ ልማት የማስተሳሰር ጽኑ ፍላጎት ማሳያ ነው። በተጨማሪም በክቀጣናው ዘላቂ የኤሌክትሪክ ገበያ ልማትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ክፍለ አሕጉራዊ ጥረት ነው።
ጥረቱ የምሥራቅ አፍሪካ የሃይል ቋት (The Eastern Africa Power Pool-EAPP) በቀጣናው ሀገራት መካከል ድንበር ተሻጋሪ የሃይል ንግድ እና የሃይል መስመር ትስስርን ለማሳለጥ እኤአ በ2005 የተቋቋመ ተቋም ግብ እውን ከማድረግ ባለፈ አሕጉራዊ ምጣኔ ሃብታዊ ትስሰርን የሚያፋጥን ነው።