የምግብ ሉዓላዊነት፤ ከተረጂነት እና ጠባቂነት መላቀቂያ መንገድ - ኢዜአ አማርኛ
የምግብ ሉዓላዊነት፤ ከተረጂነት እና ጠባቂነት መላቀቂያ መንገድ
ኢትዮጵያ ራሷን ከተረጂነት ለማላቀቅ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራች ትገኛለች። የዜጎችን የምግብ ፍላጎት በራስ የምርት አቅም የመሙላት ስራ በማከወን ከውጭ አገራት ምርት ጠባቂነት ለመላቀቅ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ውጤት እያስገኙ ነው።
ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት ከልመና ወጥታ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ውጭ ገበያ መላክ መጀመሯ ትልቅ ታሪካዊ ድል ነው። ከውጭ የኢኮኖሚ ጥገኝነት በመላቀቅ የዜጎችን የምግብ ሉዓላዊነት ለማስከበር በስንዴ ልማት የተመዘገበውን ስኬት በሌሎች የግብርና መስኮች ለመድገም በመሰራት ላይ ይገኛል።
በሩዝ፣ አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ ሻይ ቅጠልና ሌሎች የተለያዩ ሰብሎች ላይ እየተከናወነ ያለው ስራ ተጨባጭ ውጤቶች እያስገኘ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምግብ ዋስትናና በተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት ላሳዩት ርዕይ፣ የአመራር ቁርጠኝነት ከዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) የአግሪኮላ ሜዳልያ በጥር ወር 2016 ዓ.ም ያበረከተው ሽልማት ለምግብ ሉዓላዊነት ጥረት የተሰጠ እውቅና ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኢትዮጵያ መንግስት ረሃብን ሙሉ በሙሉ ከማስቀረት ባለፈ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ብሔራዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ እየሰራ መሆኑን በሽልማቱ ወቅት ገልጸው ነበር።
ኢትዮጵያ በርካታ ያልተነኩ ጥሬ ሃብቶች፣ ተስማሚ የአየር ንብረትና ለስራ ትጉ የሆነ ወጣት እንዳላት እና እነዚህን ሃብቶች ታሳቢ በማድረግ የታሪክ አውራ የሆነችውን ሀገር ልማት ወደፊት ለማራመድ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር ዋጋ እንደከፈልን ሁሉ ከምግብ ጥገኝነት ለመላቀቅ በትጋት መስራት እንደሚገባ ተናግረው ነበር።
የምግብ ሉዓላዊነት፣ የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት፣ የበጀት ሉዓላዊነት፣ ታላቁን የሀገር ሉዓላዊነት በጽናት የሚያቆሙ ናቸው። እነዚህን የሉዓላዊነት ዘርፎች ለማስከበር አዲሱ ዓይነት አርበኝነት ያስፈልገናል። ይህም የብሔራዊነት አርበኝነት መሆኑንም ከዚህ ቀደም መናገራቸው ይታወቃል።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በተመሳሳይ ኢትዮጵያ በዓድዋ ጦርነት ያስመዘገበችውን አኩሪ ድል በዘመናዊ ግብርና የዜጎችን የምግብ ሉዓላዊነት በማረጋገጥ እንደግመዋለን ሲሉ ገልጸው ነበር።
በዓድዋ የዘመኑ ጀግኖች የሀገራቸውን የግዛት ሉዓላዊነት እንዳስከበሩት ሁሉ፣ የዚህ ዘመን ትውልድ ደግሞ ሌላ የራሱን ታሪክ መጻፍ እንዳለበት አንስተዋል። በዚህ ዘመን ደግሞ የዜጎችን የምግብ ሉዓላዊነት በማረጋገጥ ድሉን ለመድገም ትልቅ ተጋድሎ እያደረገች ነው ብለዋል።
ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም
ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ያሏትን ጸጋዎች እና ሀብቶች አሟጦ በመጠቀም ከተረጂነት ተላቆ ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነች ትገኛለች። ከነዚህ ስራዎች መካከል አንዱ ከረድኤት ተቋማት ከሚደረግ የሰብዓዊ ድጋፍ ተላቆ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን እየተደረገ ያለው ጥረት ይገኝበታል።
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የሀገርን ክብርና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በራስ አቅም የሰብዓዊ ድጋፍን መሸፈን ይገባል በሚል እሳቤ አዲስ ስትራቴጂ ነደፎ እየሰራ ይገኛል። ይህ በስራ ላይ የዋለው ፖሊሲ የሀገርን ሉዓላዊ ነፃነት እና የዜጎችን ክብር በማስጠበቅ አደጋን በራስ አቅም ምላሽ በመስጠት የክምችትና የመጠባበቂያ ፈንድ አቅምን ማጎልበት የሚያስችል መሆኑን አስታወቋል።
ለዚህም ሀገር አቀፍ የስትራቴጂክ መጠባበቂያ ክምችት አቅም ከ23 በመቶ ወደ 47 በመቶ የሚያሳድጉ ዘመናዊ የክምችት መጋዘኖች እየተገነቡ መሆኑን የኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል።
ይህም የመፈጸም አቅምን በማሳደግ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን በሚል ስኬታማ የአሰራር ማሻሻያ ሥርዓት መዘርጋቱን የሚያሳይ ነው። በ2016 ዓ.ም ጸድቆ ወደ ስራ የገባው የአደጋ ስጋት አመራር ፖሊሲ ዋነኛ ማጠንጠኛው በራስ አቅም የሰብዓዊ እርዳታን መሸፈን ላይ ያተኮረ ነው።
የክልሎች ራስን የመቻል ስራዎች
ፖሊሲው የውጭ እርዳታን ብቻ ሳይሆን ክልሎች ከፌደራል መንግስት ድጋፍ ተላቀው ራሳቸውን እንዲችሉ የማድረግ አቅም መገንባት ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ የሚያመላክት ነው።
በዚሁ መሰረት ድሬዳዋና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ስድስት ክልሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ጥያቄዎችን በራሳቸው መሸፈን የሚያስችል አቅም መፍጠራቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል። በቀጣይም ሁሉም ክልሎች ራሳቸውን እንዲችሉ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጿል።
በኦሮሚያ ክልል ለመጠባበቂያ እህል ክምችት የሚውል ከ43 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በመኸርና በበጋ ወራት እርሻ በማልማት 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን የቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ መረጃ ያመለክታል።
በክልሉ ከማኅበረሰቡ የቆየ የመረዳዳት እሴት ተቀድቶ በክልሉ "ቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ" በሚል ስያሜ በተቋም ደረጃ ተቋቁሞና ሕጋዊ እውቅና አግኝቶ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን እየሰራ ይገኛል።
እየተከናወነ የሚገኘው የእርሻ ሥራ ክልሉ አሁን ላይ ያለውን 100 ሺህ ኩንታል የመጠባበቂያ እህል ክምችት ወደ 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል የሚያሳድግ መሆኑንም ተመላክቷል።
በክልሉ የምርት ማከማቻ መጋዘኖችን በሕዝብ ተሳትፎ በክልሉ በሚገኙ 21 ዞኖችና በተመረጡ ስምንት ከተሞች ላይ ለመገንባት የዝግጅት ሥራዎች ተጠናቀው ወደ ስራ ተገብቷል።
በአማራ ክልል ከተረጅነት ለመላቀቅና እርዳታን በራስ አቅም ለመሸፈን በ36 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ለመጠባበቂያ እህል ክምችት የሚውል ሰብል ለማልማት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያመለክታል።
በክልሉ በ2016/17 ምርት ዘመን ልማቱን በ36 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ለማካሄድ ታቅዶ እስካሁን ከ27 ሺህ 700 ሄክታር የሚበልጥ መሬት በመለየት ወደ ተግባር መግባቱን ቢሮው ገልጿል።
ለምርት ማሳደጊያ የሚውል 1 ሺህ 914 ኩንታል ማዳበሪያና 1 ሺህ 154 ኩንታል ምርጥ ዘር ቀርቦ ጥቅም ላይ እየዋለ እንደሚገኝም እንዲሁ።
በራስ አቅም የመጠባበቂያ እህል በማምረት ዕርዳታን ሳይጠበቅ ለችግር ለሚጋለጡ ዜጎች ተደራሽ በማድረግ ክልሉን ከተረጅነት ለማላቀቅ የተያዘው ግብ እንዲሳካ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ቢሮው አመልክቷል።
ሌላኛው የሰብዓዊ ድጋፍን በራስ የመሸፈን አቅም ጥረት ማሳያ የሲዳማ ክልል ነው። በክልሉ ለአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ የሚሆን የምግብ ሰብል ክምችት በወል መሬት የማልማት ስራ በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝ ተጠቁማለ።
በዚህም በክልሉ በመኸር እርሻ 800 ሄክታር የወል መሬት ለአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ እንዲሆኑ በተለያዩ ሰብሎች መልመካቱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የሲዳማ ክልል የተረጂነት ጉዳይ የሉአላዊነት ጉዳይ መሆኑን ከግምት በማስገባት በራስ አቅም የመጠባበቂያ ምግብ ክምችት ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑም ተመላክቷል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ሰብአዊ እርዳታን በራስ አቅም ለመሸፈን የክልሉ መንግስት የተለያዩ የልማት ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በራሱ እያለማ ያለው የሰብል ማሳ የዚሁ ስራ ማሳያ ነው። ኮሚሽኑ በዘንድሮው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ በ56 ሄክታር ማሳ ላይ በቆሎ፣ ማሽላ፣ አኩሪ አተር እና ሌሎች ሰብሎችን እያለማ እንደሚገኝ ገልጿል።
በክልሉ ሁሉም ወረዳዎች በምግብ ራስን መቻል እና ሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን በሚል መርህ የተለያዩ ሰብሎች እየለሙ መሆኑንም አመልክቷል።
ሌላኛው በተሞክሮነት የሚጠቀስ ስራ እያከናወነ የሚገኘው ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ነው። ክልሉ ለድንገተኛ የተፈጥሮ አደጋ በራስ አቅም ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም ለመገንባት ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል።
እምቅ የልማት አቅምን በመጠቀምና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን መቻል የክልሉ መንግስት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫው አድርጎታል።
በዚህም በቀጣይ ሁለት ዓመታት በክልሉ የሴፍቲኔት መርህግብር ተጠቃሚዎችን ወደ ዘላቂ ልማት በማሸጋገር ከተረጂነት የሚወጡበት ልዩ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ተገብቷል።
አረንጓዴ አሻራ እና የሌማት ትሩፋትን በማስተሳሰር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት በክልሉ ከተረጂነት ወጥቶ ራስን ለመቻል እየተደረገ ያለው ጥረት ማሳያ ናቸው።
ሌሎች ክልሎችም በራሳቸው አቅም የሰብዓዊ ድጋፍ ለመሸፈን በመስራት ላይ ይገኛሉ። ተግባራቱ ከተረጅነት ለመላቀቅና እርዳታን በራስ አቅም ለመሸፈን እየተደረገ ያለውን የባህል ለውጥ በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው።
የመውጫ ሀሳብ
በኢትዮጵያ ሰብዓዊ እርዳታ የሚሹ ወገኖችን ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል አሁናዊ በቂ የሰብዓዊ ድጋፍ ክምችትና ዝግጅት መኖሩን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
መንግስት በተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች የሚከሰቱ አደጋዎችን መቋቋም የሚያስችሉ ሀገራዊ ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አመልክተዋል።
በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች የሚከሰቱ አደጋ ስጋቶችን ለመቋቋምና ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ለመድረስ ማህበረሰቡ እርስ በርስ የሚተጋገዝበትን ስርዓት ለማጠናከር ትኩረት መደረጉንም እንዲሁ።
በሌላ በኩል የመጠባበቂያ ክምችት በመፍጠር ሰብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም በዘላቂነት ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል ሀገራዊ አቅም ለመፍጠር ወደ ስራ መገባቱንም ኮሚሽነሩ አንስተዋል።
በዚህም ካሳለፍነው ክረምት ጀምሮ እስከ በ2017/2018 የምርት ዘመን 253 ሺህ ሄክታር መሬት በማረስ 2 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ወይም 20 ሚለዮን ኩንታል ምርት በማምረት መጠባበቂያ ክምችት ለመያዝ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
እስከ አሁንም 108 ሺህ ሄክታር መሬት መታረሱን ገልፀው፤ ይህም የዕቅዱን 43 ከመቶ ይሸፍናል ነው ያሉት።
ዕቅዱን ዕውን በማድረግ እንደ ሀገር ሙሉ የመጠባበቂያ ክምችት በመያዝ በፌደራልና በክልል ደረጃ ቀዳሚ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን በመግለጽ።
በሀገር ደረጃ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት አቅም የሚፈጥሩ ናቸው።
ኢትዮጵያ ከ26 ሀገራት ለመጡ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎችን አስጠልላ ከለላና የተለያዩ መሠረታዊ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ትገኛለች።
እንደ የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት መረጃ ከሆነ በስደተኞች ስም የመጣ ማንኛውም ድጋፍ ለታለመለት ዓላማመዋሉን የመከታተልና የመቆጣጠር ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ ከዋና መሥሪያ ቤት ጀምሮ የስደተኛ ማዕከላት ድረስ የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት ዘርግቶ እየሠራ ይገኛል።
በዚህም መሠረት ሩሲያ የደቡብ ሱዳንን የእርስ በርስ ጦርነት ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ የገቡና በጋምቤላ ክልል ለተጠለሉ የደቡብ ሱዳን ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች በዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) በኩል 1 ሺህ 632 ነጥብ 4 ሜትሪክ ቶን የስንዴ ድጋፍ ትናንት አድጋለች።
የስደተኞች ሰብዓዊ ድጋፍ ከተለያዩ መንግስታትና ዓለም አቀፍ ተቋማት በሚደረግ ድጋፍ በዓለም የምግብ ፕሮግራም በኩል ሲከናወን ቆይቷል፤ የአሁኑ ድጋፍም የተደረገው ለተመሳሳይ ዓላማ እንደሆነም አገልግሎቱ አመልክቷል።
ኢትዮጵያ የአጋር አካላት ድጋፍ መቀዛቀዙን ተከትሎ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የተለያዩ አገራት ስደተኞች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ በተደጋጋሚ ጊዜ ጥሪ ማቅረቧ ይታወቃል።
ዓለም አቀፍ ረጂ አካላትም ስደተኞች ሰብዓዊ መብታቸው ተጠብቆ መሠረታዊ አቅርቦት እንዲያገኙ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸውም ስትገልጽ ቆይታለች።
በሀገር ደረጃ እየተደረጉ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት አቅም የሚፈጥሩ ናቸው።
ኮሚሽኑ የሰብዓዊ አገልግሎት፣ ዘላቂ ልማትና የሰላም ጥምረትን በማረጋገጥ ዕውቀት መር በራስ አቅም አደጋን ምላሽ የሚሰጥ ተቋም ለመገንባት የማሻሻያ እርምጃዎችን ወስዷል።
የራስ አቅም ግንባታው በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በ2030 ዓ.ም ለአደጋ ስጋት የማይበገር ማህበረሰብን ለመገንባት እቅድ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።
ሀገራዊ ትልሙ ኢትዮጵያን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ክብር፣ ነጻነት እና ሉዓላዊነት የሚያሸጋግር መልካም ጅማሮ ነው።