26ኛውን የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት የአፍሪካ አህጉራዊ ጉባኤን ኢትዮጵያ ታዘጋጃለች - ግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
26ኛውን የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት የአፍሪካ አህጉራዊ ጉባኤን ኢትዮጵያ ታዘጋጃለች - ግብርና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ጥር 7/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ 26ኛውን የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት የአፍሪካ አህጉራዊ ጉባኤ ልታስተናግድ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት ጉባኤ በየዓመቱ በግንቦት ወር በፈረንሳይ ፓሪስ የሚካሄድ ሲሆን በየሁለት ዓመቱ ደግሞ በየአህጉራቱ እንደሚካሄድ ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡
በአፍሪካ ደረጃ 25ኛው ጉባኤ እአአ በ2023 ቦትስዋና ያስተናገደች ሲሆን 26ኛውን ጉባኤ ኢትዮጵያ እንድታዘጋጅ መመረጧንም አስታውቋል።
ጉባኤው "የእንስሳት ጤና ለምግብና ስነ-ምግብ ዋስትና መረጋገጥ እና ለሕብረተሰብ ጤና" በሚል መሪ ሀሳብ ከጥር 27 እስከ 30/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡
ለጉባኤው መሳካት ከዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት ዋናው ጽህፈት ቤት፣ የአፍሪካ እና የምስራቅ አፍሪካ ተወካዮች ጋር የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች ሲደረጉ መቆየታቸውም ተገልጿል።
የግብርና ሚኒስቴርም ግብረ-ሃይል በማቋቋም ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
በጉባኤው ከየአፍካ ሀገራት የጤና ኃላፊዎችና ቋሚ ተወካዮች፣ ከዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት፣ በየአህጉሩ ያሉ የእንስሳት ጤና አመራሮች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የልማት አጋሮች፣ የግሉ ዘርፍና የመንግሥት ተቋማት ተወካዮች እንደሚታደሙም ተጠቁሟል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ(ዶ/ር) በጉባኤው በአፍሪካ የእንስሳት ጤና አገልግሎት፣ ድንበር ዘለል የእንስሳት በሽታዎችን መቆጣጠርና መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ብሎም ከበሽታ ነጻ የሆነ አህጉር ለመፍጠር የሚረዱ ውይይቶች ይደረጋሉ ብለዋል።
በጉባኤው በእንስሳት ጤናና ልማት፣ በምግብና ስነ-ምግብ ዙሪያ የሚሰሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንደሚገኙና የተለያዩ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉበት ገልጸዋል።
በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር እየተሰሩ ያሉ እንደ ዝርያ ማሻሻል፣ መኖ፣ የእንስሳት ጤና እና የሕብረተሰብ ጤና አጠባበቅ በስፋት ውይይት ይደረግባቸዋል፤ አቅጣጫዎች ይቀመጡበታል ሲሉም ተናግረዋል።
የእንስሳት ጤና በንጥረ ነገር የበለጸገ ምግብ ለማምረት እንደሚረዳ፣ መቀንጨርን ከመከላከል አንጻር የእንስሳት ጤና ምን ያህል አስተዋጽኦ እንዳለውም የምናይበት መድረክ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ጉባኤው ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራትና በአህጉር ደረጃ ካሉ ሀገራት ጋር ድንበር ዘለል የእንስሳት በሽታዎችን ለመቆጣጠር፣ የገበያ ተደራሽነትን ለማስፋት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋልም ብለዋል።
ሀገራት ያላቸውን የእንስሳት በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ስትራቴጂና ተሞክሮ፣ ኢትዮጵያም በእንስሳት ጤና፣ መሰረተ ልማት እና ያሉ መልካም አጋጣሚዎችን ለዓለም የምታስተዋውቅበት፣ ልምድ የምንጋራበት መድረክ ነው ሲሉም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
ከመቶ ዓመት የዘለለ የእንስሳት ጤና አገልግሎትና የምርምር ተቋማት፣ በእንስሳት ጤና ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ፣ ክትባትና መድሃኒት የሚያመርቱ፣ በእንስሳት ጤና የሰው ሃይል የሚያፈሩ ተቋማት መኖራቸው መልካም አጋጣሚዎች መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የሚካሄደው የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት የአፍሪካ ጉባኤ የእንስሳት ጤና እንዲጠበቅ ብሎም ዘርፉ እንዲነቃቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ማለታቸውም በመረጃው ተመላክቷል።