ኢትዮጵያ እና የሕብረቱ ወሳኝ አካል የሆነው ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና የሕብረቱ ወሳኝ አካል የሆነው ምክር ቤት
የአፍሪካ ሕብረት ቁልፍ ተቋም ነው- የሕብረቱ የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት። የፊታችን የካቲት ወር መጀመሪያ ሳምንት ላይ በሚደረገው የሕብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ከሚቀረቡ ዝርዝር አጀንዳዎች አንዱ የዚህ ምክር ቤት አባላት ምርጫ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ኢትዮጵም በቅርቡ ለምክር ቤቱ አባል ለመሆን ፍላጎቷን ይፋ አድርጋለች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የምክር ቤቱ አባል ለመሆን ያላትን መሻት በአዲስ አበባ ለሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት አምባሳደሮች አብስረዋል።
ለመሆኑ የሕብረቱ የሰላምና የደህንነት ምክር ቤት ስራው ተልዕኮና ሚና ምንድነው? አባላቱም እንደ ሀገር ምን ፋይዳ ይሰጣቸው ይሆን የሚለውን እንናስቃኝዎ!
የምክር ቤቱ ለመመስረቻ ጥንስስ የተጠነሰሰውና የማቋቋሚያ ሕግ ማዕቀፍ የጸደቀው በአውሮፓዊያኑ 2002 በደርባን(ደቡብ አፍሪካ)በተካሄደው የአፍሪካ ሕብረት መደበኛ ስብስባ ነበር። በአውሮፓዊያኑ ታኅሣሥ 2003 ወደ ስራ ገባ። ባለፈው ዓመት (ግንቦት 2016 ዓ.ም) ምክር ቤቱ 20ኛ ዓመት የምስረታ ቀኑን በአዲስ አበባ አክብሯል።
ምክር ቤቱ በአህጉሪቷ ግጭቶች እንዳይከሰቱ አስቀድሞ መከላከል፣ የግጭት አስተዳደርና አፈታት ላይ ከፍተኛ የውሳኔ ሰጪ አካል ነው። በአህጉሪቷ ለሚከሰቱ ግጭቶች ጊዜውን የጠበቀ እና በቂ ምላሽና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። ለአፍሪካ የሰላም እና ደህንነት ማዕቀፍ (African Peace and Security Architecture) ቁልፍ ምሰሶ ነው።
የምክር ቤቱ አወቃቀር፣ ተልዕኮና ሚና
ከአወቃቅር አኳያ ምክር ቤቱ ዕኩል ድምጽ ያላቸው 15 አባል አገራት ይኖሩታል። አባላቱም በሕብረቱ የስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ይመረጣሉ። በመሪዎች ጉባዔ አባልነታቸው ይጸድቃል። ከአባላቱ መካከል አምስቱ ለሶስት ዓመታተ፤ ቀሪዎቹ ለሁለት ዓመታት የሚቆይ ስልጣን አላቸው። ምክር ቋሚ አባል አገር የለም። የአባልነት ጊዜ የጨረሱ ሀገራት ግን ድጋሚ የመመረጥ መብት አላቸው።
አባላት የሚመረጡት ግን በቀጣናዊ ውክልና እና በተራ ቅደም ተከተል መርህ ነው። ይኼውም ማዕከላዊ፣ ምሥራቃዊ፣ ደቡባዊ እና ሰሜናዊ ቀጣናዎች ሶስት አባል ሀገራት ሲሆኑ የምዕራብ ቀጣና ግን አራት አባል አገራት ይኖራቸዋል።
በምክር ቤት ሕገ ደንብ መሰረት ለምክር ቤቱ አባል ለመሆን ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። ይሄውም የአፍሪካ ሰላምና ደህንነትን በማስተዋወቅና በማረጋገጥ ያለው አስተዋጽኦ፣ በቀጣናዊና በአህጉር አቀፍ ደረጃ በሰላም ማስከበር እና በሰላም መፍጠር ውስጥ ያለው ሚና፣ ቀጣናዊና አህጉር አቀፍ የግጭት መፍቻ ኢኒሺቲቮች ለመሳተፍ ያለው ፍላጎት እና ኃላፊነት ለመውሰድ ያለው ቁርጠኝነት፣ ለአፍሪካ ህብረት የሰላም ፈንድ የሚያደርገው አስተዋጽኦ፣ ለሕገ መንግስት አስተዳደር፣ የሕግ የበላይነት እና የሰብዓዊ መብቶች ያለው ከበሬታ እንዲሁም ለአፍሪካ ሕብረት የፋይናንስ መዋጮ ግዴታዎች ያለው ተገዢነት እና ቁርጠኝነት አንድን አገር አባል ሆኖ እንዲመረጥ የሚያስችሉት መስፈርቶች ናቸው።
ምክር ቤት ከሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ጋር በመጣመር ከስር የተመላከቱ ስልጣንና ተግባራቱ ተሰጥቶታል።
. ዘር ማጥፋትና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ሊያመራ የሚችል የግጭት አዝማሚያን መተንበይ፣ አስቀድሞ በመከላከልና የግጭት መንስዔዎችን ለይቶ ፖሊሲ መቀየስ። የጦር ወንጀሎች፣ ዘር ማጥፋት እና የሰብዓዊነት ወንጀሎች ሲፈጸሙ ለመሪዎች ጉባዔ ሕብረቱን ወክሎ ጣልቃ መግባት የሚችልበትን ምክረ ሀሳብ ያቀርባል።
. ለግጭቶች በሰላም እንዲፈቱ በማስቻል ሰላም መገንባት ላይ ይሰራል።የአፍሪካ ሕብረት አጠቃላይ የጋራ የመከላከያ ፖሊሲ ይተገብራል።
. ለሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ፈቃድና ስምሪት ይሰጣል፤ የሰላም አስከባሪ ኃይል የስራ ኃላፊነት ጨምሮ ተልዕኮውን የተመለከቱ መመሪያዎችን ያወጣል።
. በአፍሪካ ሕብረት አባል አገራት ኢ-ሕገመንግስታዊ የመንግስት ለውጥ ሲኖር ማዕቀብ ይጥላል።
. የፀረ-ሽብርተኝነትን ዓላም አቀፍ ስምምነቶች የአባል ሀገራት ትግበራን ይከታተላል። በመልካም አስተዳደር፣ በሕግ የበላይነት፣ የሰብዓዊ መብቶች እና መሰረታዊ ነጻነቶች እና ሰብዓዊ መብቶች ላይ ጥበቃ ያደርጋል። ቀጣናዊና አህጉራዊ የተቀናጀ የሰላምና ደህንነት አሰራርን መፈጸሙንም እንዲሁ። በጦር መሳሪያ ቁጥጥርና ትጥቅ የማስፈታት የሕግ ማዕቀፎችን ትግበራ ይደግፋል።
. የአፍሪካ ሕብረት አባል አገራትን ነጻነት እና ሉዓላዊነትን ስጋት ላይ የሚጥሉ የኃይል እርምጃዎችን በመመርመር እርምጃ ይወስዳል።
. በሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ወቅት ለሰብዓዊ ድጋፍ ያስተባብራል።
አፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የሰላምና ደህንነት የስራ ክፍል ውስጥ የሚገኘው የምክር ቤቱ ሴክሬተሪያት ለምክር ቤቱ የኦፕሬሽን ስራዎች የቀጥታ ድጋፍ ያደርጋል። ምክር ቤቱ በአህጉሪቷ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት፣ “Panel of the Wise” በተሰኘው የአፍሪካ ሕብረት የማማከር አደረጃጀት፣ በአፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል እና የሕብረቱ የሰላም ፈንድ ድጋፍ ይደረግለታል።
በምክር ቤቱ በስሩ ያሉት ወታደራዊ አባላት እና የባለሙያዎች ቡድን ኮሚቴዎች፣ የአፍሪካ የሰላምና ደህንነት ማዕቀፍ (APSA)፣ የአፍሪካ የሴቶች ግጭት መከላከል እና የሰላም ድርድር ኔትወርክ (FemWise–Africa) እንዲሁም የሰላምና ደህንነት ማስከበር ተልኮዎች ሌሎች ደጋፊ አካላት ናቸው። ምክር ቤቱ ከቀጣናዊ የኢኮኖሚ ተቋማት እና ከሌሎች ቀጣናዊ አደረጃጀቶች ጋር ግጭትን አስቀድሞ መከላከል፣ አስተዳደር እና መፍትሄ ላይ በጋራ ይሰራል።
ከተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት እና ሌሎች መሰል ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማት እንዲሁም ፓን-አፍሪካ ፓርላማ እና የአፍሪካ የሰብዓዊና የህዝብ መብቶች ኮሚሽንን ጨምሮ ከሌሎች የአፍሪካ ህብረት አደረጃጀቶች ጋር በሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ላይም በትብብር እየሰራ ይገኛል። የአፍሪካ የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት ኃላፊነቶች፣ አደረጃጀቶች እና የቅንጅት አሰራር ማዕቀፎች በአህጉሪቷ የሰላም እና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ ያለውን ቁልፍ የውሳኔ ሰጪነት አቅም የሚያሳይ ነው።
ኢትዮጵያ እና ምክር ቤቱ
ኢትዮጵያ ለመወዳደር የፈለገቸው ለሶስት ዓመት (በአውሮፓዊያኑከ2025 እስከ 2027) ድረስ ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የሕብረቱ አባል ሀገራት አምባሳደሮች ለአፍሪካ የዋለችውን ታሪካዊ ሚና ከግንዛቤ በማስገባት በውሳኔ ሂደቱ ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
በርግጥ በአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ያላት ቁልፍ ሚና ተገቢነቱ አያጠራጥርም። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ለረጅም ዘመናት በቁርጠኝነት ሰርታለች።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ ተመራማሪ ሄኖክ ጌታቸው (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና ደህንነት ምክር ቤት አባል ሆና ማገልገሏን ያስታውሳሉ። ምክር ቤቱ የአሁኑን ስያሜውን ከማግኘቱ በፊት በቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (OAU) ማዕቀፍ ከእ.አ.አ 1993 እስከ 2000 ባለው ጊዜ አባል ሆና ማገልገሏን ገልጸዋል። በአፍሪካ ሕብረት ደግሞ በአውሮፓዊያኑ ከ2004 እስከ 2010 እንዲሁም ከ2014 እስከ 2016 አገልግላለች።
ኢትዮጵያ የምክር ቤቱ አባል ሆና ብትመረጥ ብሔራዊና ቀጣናዊ ፍላጎቶቿንና ጥቅሞቿን ከማስጠበቅ እና አንጻር ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እንደምታገኝ ሄኖክ(ዶ/ር) ይናገራሉ። የምክር ቤቱ አጀንዳዎች ከብሔራዊ ጥቅሞቿ ጋር አጣጥሞ ለመሄድና ፍላጎቶቿን የሚጻረሩ ጉዳዮች ለመከላከል ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላትም በማንሳት።
የአፍሪካ ዋንኛ የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ አብዛኛውን ትኩረቱን አፍሪካ ቀንድ ከማድረጉ አንጻር ኢትዮጵያ በአካባቢው ባሉ ጉዳዮች ላይ ያላት ሚና እንዲጎለብት አስተዋጽኦ ያደርጋል ነው ያሉት ከፍተኛ ተመራማሪው። ቀጣናው ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታና ዓለም አቀፍ ትኩረትን የሚስብ መሆኑ ያሉ ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ የበኩሏን ድርሻ መወጣት እንደምትችልም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ አባልነት የሕብረቱ የመመስረቻ ቻርተርና የህግ ማዕቀፎች እንዲጠበቁ፣ አህጉራዊ አጀንዳዎችን ለማራመድ፣ ሰላምና ጸጥታን ለማስፈንና በቀጣናው ከምትጫወተው ሚና አንጻር በርካታ ጠቃሜታዎችን እንደምታገኝ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የምክር ቤቱ አባል ለመሆን የተሻለ የተወዳዳሪነት ብልጫ እንዳላት ያነሳሉ። ለምን ቢባል አንድም ኢትዮጵያ በሩዋንዳ፣ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን፣ በላይበሪያ፣ በኮንጎ፣ በሶማሊያ እና በሌሎች የአፍሪካ አገራት በሰላም ማስከበር ተሳትፎ በማድረግ ያላት ልምድ ነው። አንድም የአፍሪካ ሕብረት ዋና መቀመጫ መሆኗና ከዚህ ቀደም በምክር ቤቱ የነበራት ግልጋሎት እንደ የተወዳዳሪነት ብልጫ እንድታገኝ ያስችላታል።
አባልነቷን ለማረጋገጥ ግን ከሀገራት ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችና ሌሎች የተቀናጀ የዲፕሎማሲ ስራ ማከናወን ይጠበቃል ይላሉ። ምከር ቤቱ በሕብረቱ የሰላም እና የደህንነት ምክር ቤት የአፍሪካ የሰላምና ደህንት ጉዳዮች ከፍተኛ የውሳኔ ሰጪ አካል በመሆኑ አባል ብትሆን ካላት ታሪካዊ አበርክቶ አኳያ ይበልጥ ለአህጉራዊ ሰላምና ደህንነት ገንቢ ሚና እንደምትጫወት ዕሙን ነው።