የኢንስቲትዩቱ ስራዎች የኪነጥበብ ዘርፉ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ እንዲሰራ የሚያነሳሱ ናቸው-አርቲስቶች

አዲስ አበባ፤ጥር 16/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጅኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ያከናወናቸው ስራዎች የኪነጥበብ ዘርፉ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ እንዲሰራ የሚያነሳሱ መሆናቸውን አርቲስቶች ገለጹ።

በ2014 ዓ.ም በአዲስ መልክ የተቋቋመው ኢንስቲትዩቱ በእንጦጦ የምርምር ማዕከልና በዋና ማዕከሉ በስፔስ እና በጅኦስፓሻል ዘርፍ የሚያከናውናቸው ዐቢይ ተግባራትን በዛሬው ዕለት በኪነ ጥበብ ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሙያዎች አስጎብኝቷል፡፡

በጉብኝቱ ከተሳተፉ የኪነጥበብ ባለሙያዎች መካከል ተዋናይ ሰለሞን ሀጎስ እና አርቲስት ማህተመ ኃይሌ፥ ኢትዮጵያ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የደረሰችበትን ደረጃ መመልከታቸውን ተናግረዋል።

ባደጉት ሀገራት መጻኢ የቴክኖሎጂ ልህቀትን በሚጠቁም መልኩ የሳይንስ ፊልምና ሌሎች የኪነጥበብ ሥራዎች እንደሚሰሩ በማስታወስ፥ በእኛ ሀገርም መለመድ አለበት ብለዋል።

በጉብኝቱ የተመለከቱት ሥራ በቀጣይ የኢትዮጵያ የኪነጥበብ ዘርፍ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ የሚያነሳሳ መሆኑን ጠቅሰው፥ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚያበረክቱም ጠቁመዋል።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ቤተልሄም ንጉሴ (ኢ/ር) እንደተናገሩት፤ኢንስቲትዩቱ በስፔስ እና በጅኦስፓሻል ዘርፍ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አበረታች ሥራ እያከናወነ ይገኛል።

በሳተላይት አማካኝነት መረጃ በመሰብሰብ ለተቋማት የማድረስ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፥ ኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂ ማበልጽግና ማስፋፋት ላይ እየሠራ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡

በሳተላይት አማካኝነት የሚገኙ መረጃዎችን ለጥናትና ምርምር፣ ለግብርና ስራ፣ ለሚቲዎሮሎጂ፣ ለውሃ፣ ለመሬት እና መሰል የመረጃ አገልግሎቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የጉብኝቱ ዓላማ የኢንስቲትዩቱን ተግባራት በኪነ ጥበቡ ባለሙያዎች አማካኝነት ለህዝብ በማድረስና እንዲሁም በዘርፉ መሰማራት የሚፈልጉ ምሁራን ግንዛቤ እንዲያገኙ ለማስቻል ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም