በትግራይ ክልል አደገኛ ኬሚካሎችን የሚጠቀሙ ህገወጥ የማዕድን አውጪዎችን የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥ ልዩ ችሎት ይቋቋማል - የመሬትና ማዕድን ቢሮ

ሽረ እንዳስላሴ፤ጥር 16/2017(ኢዜአ)፡-በትግራይ ክልል በሰውና በእንስሳት ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ አደገኛና የተከለከሉ ኬሚካሎችን የሚጠቀሙ የማዕድን አውጪዎችን የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥ ልዩ ችሎት እንደሚቋቋም በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የመሬትና ማዕድን ቢሮ ገለፀ።

''ልዩ ትኩረት ለማዕድን ልማት'' በሚል መሪ ሀሳብ ክልላዊ ሲምፖዚየም በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ዛሬ ተካሂዷል።

በጊዜያዊ አስተዳደሩ የክልሉ መሬትና ማዕድን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋአለም ሐድጉ እንደገለፁት፥ በክልሉ በማዕድን ምርት ላይ የሚስተዋለውን ህገ-ወጥ ድርጊት ለመከላከልና ህጋዊ መንገድ ለማስያዝ የተቀናጀ እንቅስቃሴ በመከናወን ላይ ነው።

በማዕድን ምርት ለሰው፣ለእንስሳትና ለደን ጉዳት የሚያደርሱ የተከለከሉ አደገኛ ኬሚካሎች ጥቅም መዋሉን በጥናት በተረጋገጠባቸው ማዕድን አምራቾች ላይ የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥ ልዩ ችሎት በሽረ እንዳስላሴና በአክሱም ከተሞች ማቋቋም አንዱ ህጋዊ መስመር የማስያዝ እንቅስቃሴ መሆኑን ተናግረዋል።

በሰውና በእንስሳት ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ አደገኛና የተከለከሉ ኬሚካሎች ለማዕድን ማውጣት ተግባር እየዋሉ መሆኑ በጥናት መረጋገጡን አመልክተዋል።

በተለይ ሜርኩሪ፣ ሶድየምና ሲያናይድ የተባሉ አደገኛ ኬሚካሎችን የሚጠቀሙ ህገ-ወጥ ማዕድን አውጪዎች በስራ ላይ እንዳሉም በመቀሌና በአክሱም ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች የተደረገው ጥናት መጠቆሙን ገልጸዋል።

በፌዴራል መንግስትና በጊዜያዊ አስተዳደሩ ፈቃድ የወሰዱ በማዕድን ማውጣት ተግባር ላይ የተሰማሩ ህገ ወጦች በአስቸኳይ ከተግባራቸው እንዲታቀቡ እንደሚደረግ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ገልፀዋል።

ስለሆነም ህገወጥ የማዕድን ማውጣት እንቅስቃሴ በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ላይ ያሉ የተዛቡ አሰራሮችን በቅንጅት ማስቆም እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በተለይ በክልሉ የሚገኙ መቀሌ፣ አክሱም፣ አዲግራትና ራያ ዩኒቨርሲቲዎች በማዕድን ማውጣት ረገድ እየታየ ያለውን ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ ለማስተካከል የጀመሩትን እንቅስቃሴ ማጠናከር እንዳለባቸውም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም