ምክር ቤቱ የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግርን ለማሳካት ለሚደረገው ጥረት በልዩ ትኩረት እገዛ ያደርጋል - ምክትል አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶ

አዲስ አበባ፤ ጥር 16/2017(ኢዜአ)፡- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደ ሀገር የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግርን ለማሳካት ለሚደረገው ጥረት በልዩ ትኩረት እገዛ እንደሚያደርግ የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶ ገለጹ።

ምክትል አፈ ጉባዔዋ ይህን ያሉት በዲጂታል ቴክኖሎጂ ሽግግር ዙሪያ ለምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች በተዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ የማጠቃለያ መርሀ-ግብር ላይ ነው።

በሀገር ደረጃ ለወጣው ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ዕቅድ ስኬት በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ድጋፍና ክትትል ለማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።


 

ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ የምታደርገውን ሽግግር ዕውን ለማድረግ ከተለመደው አሰራር እና አስተሳሰብ ወጣ ባለ መልኩ ሀገርን ከፍ ለማድረግ በልዩ ትኩረት መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ3 እስከ 4 ሚሊዮን ለሚጠጉ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አስታውሰው፤ መጪውን የዲጂታል ዘመን ታሳቢ በማድረግም ክህሎታቸውን በማሳደግ በተሰማሩበት ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የተጠናከረ ድጋፍ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።

ምክር ቤቱ በሚያከናውናቸው የህግ ማውጣት፣ የህዝብ ውክልና፣ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለውን አፈፃፀም ጥንካሬና ክፍተቶችን በመለየት ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።


 

ዘርፉን በትውልድ ቅብብሎሾ አለም ከደረሰበት ደረጃ ለማድረስ ከመደበኛ ሥራ ባሻገር በትብብር እና በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ማስገንዘባቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ከምክር ቤቱ የሚጠበቀውን ኃላፊነት በመወጣት ከዘረፉ የሚጠበቁ ውጤቶችን ለማስመዝገብ እንሰራለን ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም