የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ተግባራዊ መደረጉ ሕብረተሰቡ በዲጂታል ኢኮኖሚ ላይ ያለው እምነት እንዲጨምር አድርጓል

አዲስ አበባ፤ ጥር 17/2017(ኢዜአ)፡- የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ተግባራዊ መደረጉ ሕብረተሰቡ በዲጂታል ኢኮኖሚ ስርዓቱ ላይ የነበረው እምነት እንዲጨምር ማድረጉን የአዲስ አበባ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ አስታወቀ።

“ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” ስትራቴጂ በዋናነት የዲጂታል መሰረተ ልማት በመገንባትና በማስፋፋት የሀገሪቱን የምጣኔ ሀብት እድገት ማፋጠንን ዓላማ ያደረገ ነው።

ስትራቴጂው ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት አመታት የሚቆይ ሲሆን ዘንድሮ የመጀመሪያው ዙር ይጠናቀቃል።

የአዲስ አበባ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰለሞን አማረ ለኢዜአ እንደገለጹት የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ህብረተሰቡ በዲጂታል ኢኮኖሚና ግብይት ላይ የነበረው ንቃተ ህሊና እንዲያድግ አድርጓል።


 

በተለይም የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች፣ የነዳጅ ግብይት፣ የመብራት፣ የቤት ኪራይ፣ የውሃና ሌሎች ክፍያዎችን ከመፈፀም አንፃር ስትራቴጂው የማህበረሰቡን መጉላላት ማስቀረቱን ጠቅሰዋል።

የአየር ትኬቶችን ጨምሮ ትልልቅ የትራንስፖርት አገልግሎቶች በዲጂታል ቴክኖሎጂ መሰጠቱ ህብረተሰቡ በቴክኖሎጂው ላይ እምነት እንዲያሳድር አድርጓል ነው ያሉት።

ባለፉት አምስት አመታትም ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ ከማድረግና ከመጠቀም አንፃር ከፍተኛ ለውጥ መታየቱን ጠቅሰዋል።

በመዲናዋ በአሁኑ ወቅት ከ400 በላይ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በዲጂታል ኢኮኖሚ ስርዓት ውስጥ ገብተው ጥቅም ላይ መዋላቸውንም ነው አቶ ሰለሞን ያነሱት።

ከዚህ ውስጥም የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ፣ የመንጃ ፈቃድ፣ የመሬት እና የሲቪል ማህበረሰብ ምዝገባና የማህበረሰብ አገልግሎቶች ተጠቃሽ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም