በክልሉ የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎች የአርሶ አደሩን ምርታማነት ጨምረዋል- አቶ ሄኖክ ሙሉነህ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎች የአርሶ አደሩን ምርታማነት ጨምረዋል- አቶ ሄኖክ ሙሉነህ
አዲስ አበባ፤ጥር 17/2017 (ኢዜአ)፡-በሐረሪ ክልል በተፋሰስ ልማት ስራዎች የአርሶ አደሩን ምርታማነት መጨመር መቻሉን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሄኖክ ሙሉነህ ገለጹ።
በሐረሪ ክልል "የአፈር ሀብታችን ለብልፅግናችን" በሚል መሪ ቃል የተፋሰስ ልማት ስራ ዛሬ ተጀምሯል።
የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሄኖክ ሙሉነህ የተፋሰስ ልማት ስራውን አስጀምረዋል።
አቶ ሄኖክ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በተፋሰስ ልማት ስራው ላይ ከ30 እስከ 40 ሺህ አርሶ አደሮች ይሳተፋሉ።
በክልሉ ከዚህ ቀደም የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎች የከርሰ ምድር ውሃ ተጠቃሚነትን በመጨመር በማድረግ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ማሳደግ መቻሉን አመልክተዋል።
ተራቁተው የነበሩ ተራራዎች በደን እንዲሸፈኑ በማድረግ የተከናወነው ስራ ለትውልድ የለማና አረንጓዴ አካባቢ ለማስረከብ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።
ከለውጡ ወዲህ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መደገፋቸው፤ ተራቁተው የቆዩ መሬቶች በፍጥነት እንዲያገግሙ ማስቻሉን ጠቁመዋል።
በዚህም አርሶ አደሩ የመስኖ ልማት ስራውን በማጎልበት የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ ነው ኃላፊው የገለጹት።
አርሶ አደሩ የተፋሰስ ልማት ስራዎችን ውጤት በተጨባጭ መመልከቱ የተሻለ የስራ ባህልን በመላበስ ከግብርና ስራው ጎን የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን በስፋት እንዲያከናውን ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አብራርተዋል።
የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን በማከናወን የተፈጥሮ ሀብትን ጠብቆ ለም መሬትን ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ የሁሉም ኃላፊነት ነው ያሉት አቶ ሄኖክ፥ በዚህም ማህበረሰቡ በተፋሰስ ልማት ስራው ላይ በነቂስ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።
የሐረሪ ክልል ግብርና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ነስረዲን አህመድ በክልሉ በ16 ተፋሰሶች ላይ ከ900 ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት በዕቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኝ መግለጻቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።