በተለያዩ የግብርና መስኮች የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በተለያዩ የግብርና መስኮች የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
አዳማ ፤ጥር 17/2017(ኢዜአ)፡-የሰብል ልማትን ጨምሮ በተለያዩ የግብርና መስኮች የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸው ተገለጸ።
በግብርና ሚኒስቴር የአካባቢና አየር ንብረት ለውጥ ማስተባበሪያ ቡድን መሪ አቶ አዲሱ ነጋሽ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ ስር ኢትዮጵያ የተለያዩ እቅዶችን፣ ስትራቴጂዎችንና የማስፈፀሚያ ስልቶችን አዘጋጅታ እየተገበረች ትገኛለች።
"እንደ አገር በሰብል፣ በእንስሳት ልማትና እፅዋት ላይ እየሰራን እንገኛለን" ያሉት ቡድን መሪው፤ በተለይ በአርብቶ አደሩ አካባቢ የእንስሳት ዝሪያን በማሻሻልና ምርታማነቱን በመጨመር የሙቀት አማቂ ጋዞች መጠንን ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
በዚህም የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ የኑሮ ሁኔታ በማሻሻል በአካባቢው ላይ በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቋቋም የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
ስርዓተ ምግብን ለማረጋገጥ በቆላማ የአገሪቷ አካባቢዎች የፀሃይ ሃይልን በመጠቀም አነስተኛ መስኖን በማስፋፋት፣ ሰብልና የእንስሳት መኖን በማምረት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ እየተሰራባቸው ካሉ ፕሮጀክቶች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በተፈጥሮና በሰው ስራሽ አደጋዎች የተጎዱና የተራቆቱ መሬቶች ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነፃ በማድረግ እንዲያገግሙና ወደ ምርት እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ካሏት 12 ተፋሰሶች ውስጥ ዘጠኙ ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞች መሆናቸውን ጠቁመው፤ የውሃ መጠናቸው እንዲጨምር፣ የአፈር መሸርሸርና የመሬት መራቆትን ለመቀነስ የተፋሰስ ልማት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
በተለይ በሰብል፣ በወተትና ወተት ተዋፅዖ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በአፈርና ውሃ እቀባ፣ በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብሮች እውቅና የተገኘባቸው ፕሮጀክቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
የድህረ ምርት ብክነትን ለመቀነስና በምግብ ራስን ለመቻል የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂን ተደራሽ በማድረግ የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ በአርብቶና አርሶ አደሩ አካባቢ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቋቋም ቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ስራዎች እየተከናወኑ ካሉት ፕሮጀክቶች መካከል መሆኑንም አስረድተዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በፋይናንስና አቅም ግንባታ ከሚደግፉ ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥና ማቋቋሚያ ፈንድ ጋር ፕሮጀክቶችን በመቅረፅና ፋይናንስ በማስፈቀድ በትብብር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን መቀነስ የሚያስችሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅና ሀብት በማፈላለግ በመደበኛነት ከሚሰራው የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋሚያ ስራዎች በተጨማሪ ሌሎች ስራዎች በፕሮጀክት እየተሰሩ መሆኑንም አመልክተዋል።