በክልሉ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት የተገኘው ውጤት ህብረተሰቡ በነቂስ ወጥቶ ሥራውን እንዲያጠናክር ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት የተገኘው ውጤት ህብረተሰቡ በነቂስ ወጥቶ ሥራውን እንዲያጠናክር ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል
ከሚሴ፤ጥር 17/2017(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት የተገኘው ተጨባጭ ውጤት ህብረተሰቡ በነቂስ ወጥቶ ሥራውን ይበልጥ እንዲያጠናክር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ሥራ በአርጡማ ፉርሲ ወረዳ ወገሬ ደበሶ ቀበሌ ቦሩ ተፋሰስ ዛሬ ተጀምሯል።
በማስጀመሪያው መረሃ ግብር ላይ የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው እንደገለጹት ፤ በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ሥራ በተጨባጭ አበረታች ውጤት አስገኝቷል።
ይህም የተራቆቱ ተራራዎች ማገገማቸውን፣ የደን ሽፋኑ፣ ምርታማነት የአፈር ለምነትና እርጥበት ከመጨመሩ ባለፈ ተፋሰሶችን ዘላቂ በማድረግ ለወጣቶች የሥራ እድል መፍጠሪያ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
በልማቱ የተገኘው ተጨባጭ ውጤት ህብረተሰቡ በየዓመቱ ያለ ቀስቃሽ በራሱ ተነሳሽነት በነቂስ ወጥቶ እንዲሰራና ዘላቂ እንዲያደርግ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስታውቀዋል።
ተግባሩን አላቂ በማድረግ ለወጣቱ የሥራ እድል በመፍጠር ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት የሚደረገው ጥረትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ዘንድሮም በተመረጡ ተፋሰሶች የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን ዝግጅት ተደርጎ ሥራው በክልል ደረጃ መጀመሩን ገልጸዋል።
ተፋሰሶችን ከአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ጋር በማስተሳሰር የተሻለ ጥቅም እንዲሰጡ ለማድረግ ችግኞች እየተዘጋጁ ነው ብለዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ አሊ በበኩላቸው፥ ዞኑ ውሃና ዝናብ አጠር በመሆኑ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ የህልውና ጉዳይ ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም ባለፉት ዓመታት በዞኑ የተከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ አበረታች ውጤት ማስገኘቱን ተናግረዋል።
ተፋሰሶችን በአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች በመትከል ለወጣቶችም የሥራ እድል እየተፈጠረ መሆኑን አብራርተዋል።
በዞኑ ህብረተሰቡን በማሳተፍ በተለዩ ስፍራዎች የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን ዛሬ ወደ ተግባር መገባቱን የተናገሩት ደግሞ የዞኑ ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ሀሰን ሰይድ ናቸው።
ቀደም ሲል በተከናወነ ተግባራት የተጎዱ አካባቢዎችና ተራሮች ማገገማቸውን፣ ምርታማነት መጨመሩ፣ የደን ሽፋኑ መጨመሩንና የአፈር ለምነት መጠበቁን ገልጸዋል።
በአርጡማ ፉርሲ ወረዳ የወገሬ ደቢሶ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር እንድሪስ ጀማል በሰጡት አስተያየት፤ ቀደም ሲል በተከናወነ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ሥራ በተጨባጭ ተጠቃሚ በመሆናቸው ዘንድሮም በነቂስ ወጥተው ልማቱን መጀመራቸውን ተናግረዋል።
በማስጀመሪያው መረሃ ግብር ላይ የክልል የዞን፣ የወረዳና የከተማ አመራር አባላትን ጨምሮ ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።