በክልሉ የተፋሰስ ልማት ስራው የመሬት ለምነትን በመጨመሩ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ተጠቃሚ ሆነናል - የአካባቢው አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የተፋሰስ ልማት ስራው የመሬት ለምነትን በመጨመሩ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ተጠቃሚ ሆነናል - የአካባቢው አርሶ አደሮች
ሐረር፤ ጥር 17/2017(ኢዜአ)፡- በሐረሪ ክልል የተፋሰስ ልማት ስራው የመሬት ለምነትን በመጨመሩ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው የአካባቢው አርሶ አደሮች ገለጹ።
የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራው በግብርናው ዘርፍ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጡ ምክንያት መሆኑንም የክልሉ ግብርና ልማት ቢሮ ገልጿል።
በክልሉ የተፋሰስ ልማት ስራ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አንጻር አበርክቶው የላቀ በመሆኑ በየዓመቱ የበጋ ወቅት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች በስፋት ይከናወናሉ።
በክልሉ ኤረር ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ኢብራሂም አብዱሌ እንደተናገሩት በክልሉ የሚከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎች የአፈር ለምነትን በመጨመርና የከርሰ ምድር ውሃን በማጎልበት ምርትና ምርታማነታችን እንዲጨምር አድርጓል።
በተለይ በተፋሰሱ ላይ የምናከናውነው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ስራ አካባቢውን ከሞቃታማነት ወደ ነፋሻማነት መለወጡን ተናግረዋል።
የተፋሰስ ልማት ስራ የተራቆቱ አካባቢዎች አረንጓዴ እንዲሆኑና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው ያሉት ደግሞ ሴት አርሶ አደር ፋጡማ ሙሜ ናቸው።
በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ በተገኘው የከርሰ ምድር ውሃ አትክልትና ፍራፍሬን በማልማት ተጠቃሚነታችንን እያረጋገጥን እንገኛለን ብለዋል።
የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራው በግብርናው ዘርፍ ለሚያከናወኑት የልማት ስራዎች ተጨባጭ ለውጥ መምጣት ምክንያት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ነስረዲን አህመድ ናቸው።
በተለይ ባለፉት ዓመታት በተሰሩ የተፋሰስ ልማት ስራዎች አንድ ጊዜ ብቻ ሲያመርቱ የነበሩ አርሶ አደሮች በዓመት እስከ ሶስት ጊዜ ማምረት እንዲችሉ አስችሏል ብለዋል።
በክልሉ ለ30 ቀናት በሚቆየው የተፋሰስ ልማት ስራም ዛሬ መጀመሩን ጠቁመው በዚህም በ16 ተፋሰሶች ላይ 900 ሄክታር መሬት የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ዕቀባ ስራ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
በተፋሰስ ልማት ሥራው ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሔኖክ ሙሉነህ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት የተሰሩት የተፋሰስ ልማት ስራዎች በግብርና ምርትና ምርታማነት መጨመር ላይ ተጨባጭ ውጤት እያመጡ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ላይ የተሰሩ ስራዎች የአርሶ አደሩን የስራ ባህል እየለወጡ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በሐረሪ ክልል "አፈራችን ለሀገራዊ ብልጽግናችን" በሚል መሪ ሃሳብ የዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ስራ መጀመሩ መገለጹ ይታወሳል።