የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በማጎልበት ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ራስን መጠበቅ ይገባል - ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ

አዲስ አበባ፤ ጥር 18/2017(ኢዜአ)፦ ዜጎች የጎዳና ላይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በማጎልበት ራሳቸውን ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ሊጠብቁ እንደሚገባ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ አሳሰቡ።

የጤና ሚኒስቴር ከአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጋር በመተባበር ያዘጋጁት "የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለጤናማ እናትነት" በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተካሂዷል።

በመርሀ ግብሩ የጤና የሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ወጣቶች ተሳትፈዋል።

የእናትነት ወርን ምክንያት በማድረግ ዛሬ የተካሄደው ስፖርታዊ እንቅስቃሴው ከቶታል ሶስት ቁጥር ማዞሪያ እስከ አለርት ኮምፕሬሄንሲቭ ሆስፒታል የእግር ጉዞ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተደርጓል።

ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በአካል ብቃት የዳበረ ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር መንግሥት በትኩረት እየሰራ ነው።

ማህበረሰቡን ያሳተፈ የአካል ብቃት እንቅስቃሴም የዚህ አካል መሆኑን ጠቁመው፤ እናቶች ጤናቸውን በአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያጎለብቱ ጠይቀዋል።

ዜጎች የጎዳና ላይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በማጎልበት ራሳቸውን ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ሊጠብቁ ይገባልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም