ከአንድ ሺህ በላይ ስታርትአፖች ክህሎት መር ዓለም አቀፍ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
ከአንድ ሺህ በላይ ስታርትአፖች ክህሎት መር ዓለም አቀፍ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ ጥር 18/2017(ኢዜአ)፦ ከአንድ ሺህ በላይ ለሚሆኑ ስታርትአፖች ክህሎትን መሰረት ያደረገ ጥራት ያለውና ዘላቂ ዓለም አቀፍ የሥራ ዕድል መፈጠሩን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቪሽን ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት የስራ ዕድል የሚፍጥሩ ሀገር በቀል ኩባንያዎችን ለማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ናቸው፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ(ዶ/ር) እንደገለጹት በመንግስት ወጣቶችና ታዳጊዎች ያላቸውን ተሰጥኦ እንዲያወጡ የተሰራው ስራ ውጤታማ ነው፡፡
ለዚህም ምቹ ምሕዳር መፍጠር የተቻለ መሆኑን ገልጸው፤ እስካሁን ባለው ሂደትም ተሰጥኦን በመለየት፣ በማልማት፣ በማሳደግና በማበልጸግ ወደ ምርትና አገልግሎት የመቀየር ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የሳይንስና ቴክኖሎጂ እና የምርምር ተቋማት ሚናቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
በመንግስት በኩልም እንደ 5ጂ ያሉ አስፈላጊ የመሰረተ ልማትና በፖሊሲ የታገዘ የድጋፍ ማዕቀፍ ተዘጋጅተው ተግባራዊ መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
በተዘረጉ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶች ለመጠቀም ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸው፤ ለአብነትም በኔትዎርክ ማስፋፋት ስራ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ ኢ-ኮሜርስ፣ ኢ-ፋይናስና መሰል ለኢኮኖሚና ለሰው ሃብት ልማት ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በዚህም ክህሎትን መሰረት ያደረገ ጥራት ያለው፣ ዘላቂና አስተማማኝ ዓለም አቀፍ የስራ ዕድል እየተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
ከስድት አመት በፊት 50 የነበሩት ስታርትአፖች በአሁ ወቅት ከአንድ ሺህ በላይ መድረሳቸውን ጠቅሰዋል።
ከነዚህም መካከል ከ92 በላይ የሚሆኑት ተጨማሪ ሃብትና የስራ ዕድል መፍጠር የቻሉ መሆናቸውን አንስተዋል።
በስታርትአፖች የተፈጠሩ የስራ ዕድሎች በዋነኛነት በፋይናስ ቴክኖሎጂ፣ በአግሪ ቴክ (በግብርና)፣ በአገልግሎት፣ በትራንስፖርት፣ በአይሲቲ፣ በኢንዱስትሩ፣ በቱሪዝምና በሌሎች መሰል ዘርፎች መሆኑን አንስተዋል፡፡
በዘርፎቹ መተግበሪያዎችን በማልማት የኢ-ኮሜርስ የንግድ መተግበሪያዎችን እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም በዕውቀት የሚመራ ሀገራዊ ኢኮኖሚ ለመገንባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል፡፡
በግብርናው ዘርፍም የእንስሳት ጤናን ለመጠበቅ የሚያስችል ክትባት በባዮቴክኖሎጂ ምርምር ዘርፍ በማምረት ከውጭ የሚገባን ምርት የመተካት በጎ ጅምር በስታርትአፖች እየታየ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ከኮዲንግ ኢንሼቲቭ አንጻር የኮምፒውተር ቋንቋ በአግባቡ የሚረዳ፤ የተረዳውንም ወደ ጽሁፍ የሚቀይር መተግበሪያ በማበልጸግ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂ ማልማት የሚችሉ ወጣቶችን የማፍራት ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ወጣቶች በኮዲንግ ኢንሼቲቭ ስልጠና የላቀ አግልግሎት መስጠት የሚያስችል የዲጂታል ዕውቀት በተለያዩ ተቋማት ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡
ወጣቶቹም እየተሰጠ ያለውን የኮዲንግ ስልጠና ዕድል በአግባቡ እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡