በድሬዳዋ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ በይፋ ተጀመረ

ድሬዳዋ፤ ጥር 18/2017(ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርየዘንድሮ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።

የተፋሰስ ልማት ሥራው "የአፈር ጥበቃ ስራችን ለብልፅግናችን" በሚል መሪ ሃሳብ በ38 የገጠር ቀበሌዎች ላይ ተጀምሯል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፈትህያ አደንና ከንቲባ ከድር ጁሃር ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች የተፋሰስ ስራዎችን አስጀምረዋል።

የድሬዳዋ ግብርና፣ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኑረዲን አብደላ እንደተናገሩት፤ ዛሬ በተጀመረውና ለአንድ ወር በሚዘልቀው የተፋሰስ ልማት ሥራ 5 ሺህ 550 ሄክታር የተራቆቱ አካባቢዎች የአፈርና የውሃ ጥበቃ ይከናወናል።

የገጠር መንገድ ጥገና፣ የመስኖ ውሃና የማሳ እንክብካቤ፣ የጤና እና የትምህርት ተግባራትን ከፍ የሚያደርጉ ስራዎች ይተገበራሉ ብለዋል።

የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው የመሬት መራቆትን የሚቀንስና በጎርፍ የሚወሰድን 48 ሺህ 700 ቶን ለም አፈር የሚታደግ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአንድ ወር በሚቆየው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ላይ 41 ሺህ 300 የሚሆኑ የአስተዳደሩ ነዋሪዎች በባለቤትነት እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።

የብዬ አዋሌ ገጠር ወረዳ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ያሲን መሐመድ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት የአካባቢውን ስነምህዳር ከመለወጥ በተጨማሪ ለምርታማነት እና ለኑሮ ምቹ አካባቢ መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል።

እነዚህን የተገኙ ውጤቶች በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል ህብረተሰቡ በነቂስ ወጥቶ በልማቱ ላይ መሳተፍ ጀምሯል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም