የተፋሰስ ልማቱ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የሚደረገውን ሽግግር እያገዘ ነው- ከንቲባ ከድር ጁሃር - ኢዜአ አማርኛ
የተፋሰስ ልማቱ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የሚደረገውን ሽግግር እያገዘ ነው- ከንቲባ ከድር ጁሃር
ድሬዳዋ፤ ጥር 18/2017(ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የሚከናወነው የተፋሰስ ልማት ስራ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገርና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እያገዘ መሆኑን የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር ተናገሩ።
" የአፈር ጥበቃ ስራችን፤ ለብልፅግናችን" በሚል መሪ ሀሳብ በድሬዳዋ 38 የገጠር ቀበሌዎች የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
የተፋሰስ ልማቱን በአራቱ የገጠር ክላስተሮች ተሰማርተው ያስጀመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር እና የአስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ናቸው።
በብዮ አዋሌ ክላስተር ተገኝተው የተፋሰስ ልማቱን ያስጀመሩት ከንቲባ ከድር ጁሃር በወቅቱ እንደተናገሩት፤ አገራዊውን ለውጥ ተከትሎ በድሬዳዋ ውጤቶች ከተመዘገበባቸው ልማቶች መካከል የተፋሰስ ልማት አንዱ ነው።
በአስተዳደሩ በህዝብ ንቅናቄ የተሰሩት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ከተረጂነት ወደ አምራችነት ለመሸጋገር የሚከናወኑ ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ማገዙን ገልጸዋል።
እንደ ከንቲባ ከድር ገለፃ በዘንድሮ የተፋሰስ ልማት ከሚከናወነው የአፈርና የውሃ ጥበቃ ስራ ጎን ለጎን የበጋ ወራት የበጎ ፍቃድ ተግባራት በትኩረት ይተገበራሉ።
በመሆኑም ሁሉም በትጋት እንዲተገብረው ጥሪ አስተላልፈዋል።
የአስተዳደሩ ግብርና፣ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኑረዲን አብደላ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በ50 ሺህ ሄክታር የተራቆቱ ተፋሰሶች ላይ የአፈርና የውሃ ጥበቃ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።
የተከናወኑት ልማቶች የጎርፍ ተጋላጭነት እና የአፈር መጠረግን በመከላከል በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥና የስራ ዕድል ለመፍጠር እያገዙ ይገኛሉ ብለዋል።
በተፋሰስ ልማቱ ላይ እየተሳተፉ ከሚገኙት አርሶአደሮች መካከል ወጣት አብዱልናስር ሙክታር ባለፉት ዓመታት የተሰሩት ልማቶች የጠፉ ምንጮችና የተፈጥሮ ደኖች እንዲመለሱ ማገዙን ተናግረዋል።
ወጣቶች ተደራጅተው ልማቱን በመጠበቅ የእንሰሳት መኖ በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው የዘንድሮውን ዕቅድ ለማሳካትም እንደሚተጉ ገልጸዋል።