ኢትዮጵያ በአካታች የዲጂታል መሠረተ ልማትና ኢኮኖሚ ግንባታ ፈጣን ለውጥ እያስመዘገበች ነው -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ጥር 19/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ከለውጡ ማግስት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን በመተግበር አካታች ኢኮኖሚ ለመገንባትና የመንግሥት አገልግሎትን ለማሻሻል ወሳኝ መሠረት ማስቀመጧን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞን የተመለከተ ኤግዚቢሽንና አውደ ጥናትን በሳይንስ ሙዚየም በይፋ አስጀምረዋል።

ኢትዮጵያ ከለውጡ ማግስት የቴክኖሎጂ ዕድገት ዕድሎችን ለመጠቀም እና ፈተናዎቹን ለማለፍ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን እየተገበረች እንደምትገኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

መንግስት የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት ወሳኝ መሰረተ ልማት ማስፋፋቱን የጠቀሱት አቶ ተመስገን፥ የህግ እና የአሰራር ማዕቀፎችን ስራ ላይ በማዋል የመንግሥት ተቋማት አገልግሎትን በዲጂታል የማዘመንና ለዜጎች ፈጣንና ውጤታማ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል።

በስትራቴጂው የትግበራ ዓመታት የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎትና ክፍያ እንዲሁም የኤሌክትሮኒክ ንግድ በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን አንስተዋል።

የግሉ ዘርፍ የዳታ ማዕከላትን በማስፋፋት እና አዳዲስ የዲጂታል አገልግሎቶችን በማቅረብ ረገድ ያለው ተነሳሽነትና አስተዋጾም በእጅጉ ጨምሯል ነው ያሉት።

በዚህም ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ መሰረት የጣሉ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ከተለዩ ቁልፍ የዲጂታል መሠረተ ልማቶች ውስጥ ዋነኛው በ2014 ዓ.ም መተግበር የጀመረው ዲጂታል የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ነው ብለዋል፡፡

ባለፉት የትግበራ ዓመታትም በሀገሪቱ ከ1 ሺህ በላይ የምዝገባ ጣቢያዎችን በመክፈት ከ11 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች በላይ መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

መንግሥት የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ካውንስል በማቋቋም የዲጂታል ሽግግሩ የተቀናጀ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ የሃብት ብክነትን የማያስከትል፣ የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ እና ፈጣን ለውጥ የሚያመጣ እንዲሆን እየሠራ ነው ብለዋል።

ሽግግሩን የሚያፋጥኑ የዲጂታል መንግስት ስትራቴጂ እና የኤሌክትሮኒክ ንግድ ስትራቴጂዎች የተዘጋጁ ሲሆን በቅርቡ ፀድቀው ወደ ሥራ እንደሚገቡም ጠቁመዋል።

ስትራቴጂዎቹ የአገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል፣የንግድ አሰራርን በማዘመን እና የበለጠ አሳታፊ እና ዲጂታል ማህበረሰብ በመፍጠር ረገድ የሚኖራቸዉ ሚና ከፍተኛ እንደሆነም ገልጸዋል።

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የመጨረሻው የስትራቴጂው ትግበራ ዓመት ላይ መሆኑን በማንሳት፥ በቀጣይ እስከ 2030 የሚተገበር የ5 ዓመታት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን ለማውጣት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም