ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ መሰረት የጣሉ ተግባራት ተከናውነዋል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ጥር 19/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ መሰረት የጣሉ ተግባራት ተከናውነዋል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ዛሬ የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ እና ውጥኖችን የተመለከተ ኤግዚቢሽንና ዐውደ ጥናት አካሂደናል ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል።

መንግሥት ከለውጡ ማግሥት 2012 ዓ.ም ጀምሮ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ሀገራችን የቴክኖሎጂ ዕድገት ዕድሎችን እንድትጠቀም የሚያስችሉ ተግባራትን አከናውኗል ብለዋል።

የዲጂታል መሠረተ ልማት በመሥፋፋቱ የፋይናንስና የክፍያ ስርዓት በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ መሆኑን ተናግረዋል።

የመንግሥት አገልግሎቶችን የማዘመንና ወደ ዲጂታል የማሸጋገር እንዲሁም የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ መጨመሩንም ገልጸዋል።

የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስራዎች የተቀናጁ፣ ደህንነታቸው የተጠበቀ፣ የሃብት ብክነትን የማያስከትሉ፣ የዜጎቻችንን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡና ፈጣን ለውጥ የሚያመጡ እንዲሆኑ መንግሥት የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የመጀመሪያውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትግበራ እያጠናቀቅን በመሆኑም በቀጣይ 5 ዓመታት ስራ ላይ የሚውል የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ዝግጅት እያጠናቀቅን እንገኛለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም