የታዳጊ ወጣቶች የምዘና ውድድር በሚቀጥለው ሳምንት ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የታዳጊ ወጣቶች የምዘና ውድድር በሚቀጥለው ሳምንት ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ጥር 19/2017(ኢዜአ)፦ስምንተኛው ዙር የታዳጊ ወጣቶች የምዘና ውድድር በሚቀጥለው ሳምንት በወላይታ ሶዶ ከተማ እንደሚካሄድ የባህልና ስፓርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የታዳጊ ወጣቶች የምዘና ውድድር "የታዳጊ ስፖርተኞች ልማት ለአሸናፊ አገር" በሚል መሪ ሃሳብ በወላይታ ሶዶ ከተማ እንደሚካሄድ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገልጿል።
በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሀመድ እንደገለፁት፤መንግስት ለስፖርቱ ዘርፍ እድገት ትኩረት ሰጥቷል።
በተለይም ከለውጡ በኋላ እየተሰሩ ያሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች ለስፖርቱ ዘርፍ ትልቅ ትኩረት መሰጠቱን የሚያመላክት ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
በወላይታ ሶዶ ከተማ በሚካሄደው ውድድር ላይ እግር ኳስ፤አትሌቲክስ፤ ፤ውሃ ዋና፤ማርሻል አርትን ጨምሮ በ11 የስፖርት አይነቶች ምዘናው ይካሄዳል።
2 ሺ 656 ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉበት የታዳጊ ወጣቶች ውድድርም ከጥር 27 እስከ የካቲት 5 ቀን 2017 እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።
ውድድሩ የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና ፕሮግራምን ጥራት እና ውጤታማነት በመመዘን ክፍተቶችን መለየት አላማ አድርጎ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል፡፡
በውድድሩ የሚለዩ ተተኪ ስፖርተኞች ወደ ክለቦችና የስፖርት አካዳሚዎች የሚገቡበትን እድል ለመፍጠር እንደሚያስችልም አብራርተዋል።
በሚኒስቴሩ የስፖርት ልማት ዘርፍ መሪ ስራ አስፈፃሚ ተስፋዬ በቀለ በበኩላቸው፤ተቋርጦ የቆየው የታዳጊ ወጣቶች የምዘና ውድድር በተለይም ስፖርቱን ለማነቃቃት የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡
በተለይም ውድድሩ በወላይታ ሶዶ መካሄዱ ያሉትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ለማነቃቃት በር እንደሚከፍት ነው የጠቀሱት፡፡
ከዚህ ባለፈ ከሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ታዳጊዎች የሚሳተፉበት በመሆኑ እርስ በርስ ይበልጥ የሚተዋወቁበትን መድረክ ይፈጥራል ብለዋል።