ኢንስቲትዩቱ እርጎን ከ10 ቀናት በላይ ሳይበላሽ ማቆየት የሚያስችል እርሾ አመረተ

አዲስ አበባ፤ ጥር 19/2017(ኢዜአ)፦ የባዮ እና ኢመርንጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ወተትን በሰዓታት ውስጥ ማርጋትና እርጎን ከ10 ቀናት በላይ ሳይበላሽ ማቆየት የሚያስችል እርሾ ማምረቱን ይፋ አደረገ፡፡

ከፍተኛ የቁም እንስሳት ሀብት ባላት ኢትዮጵያ ወተትን በነፍስ ወከፍ የመጠቀም ምጣኔ በዓመት ከ19 ሊትር አይበልጥም።

በዚህም መንግስት የወተት ኃብት ልማት ስትራቴጂ ነድፎ የሌማት ትሩፋትን ጨምሮ የወተት ምርታማነትንና የነፍስ ወከፍ ፍጆታን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራትን በትኩረት እየሰራ ነው።

የወተት ልማቱን ማሳደግ፣ የወተት ምርት ላይ እሴቶችን መጨመር እና የምርት ጥራትና ደኅንነት ማስጠበቅ ላይ ትኩረት ተሰጥቷል።

በዘርፉ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማስፋት የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ከተቋቋሙት ተቋማት መካከል የባዮ እና ኢመርንጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አንዱ ነው፡፡

የኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ ተስፋማሪያም በርሔ(ዶ/ር) እንደሚገልጹት የወተት ምርት አያያዝና አጠባበቅ አንዱ የትኩረት መስክ ነው።

በዚህም ኢንስቲትዩት ባደረገው ሳይንሳዊ ምርምር ባወጣው ስድስት አይነት የእርጎ እርሾዎች ወተትን በፍጥነት ማርጋትና ደህንነቱ ተጠብቆ እንዲቆይ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

ባክቴሪያዎች ወተትን እንዲረጋም፤ እንዲበላሽም መንስኤ እንደሆኑ ገልፀው፤ እርሾው ወተት በሰዓታት ውስጥ ረግቶ ግን ለቀናት ሳይበላሽ እንዲቆይ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት ወተት ለመርጋት እስከ አራት ቀን የሚወስደውን ጊዜ ከአራት እስከ ስድስት ሰዓት ማሳጠር መቻሉን ገልጸዋል።

የእርጎ እርሾ እርጎ ሳይበላሽ ከ10 ቀናት በላይ ማቀየት የሚያስችል መሆኑንም ገልጸው፤ ይህን የዜጎችን ጤና ከመጠበቅ ባለፈም ብክነት ለመከላከል የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የምርምር ውጤቱ በግልና በኢንዱስትሪ ዕርጎ ለሚያመረቱ አምራቾች ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኩባንያዎች ከባዮ እና ኢመርንጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር ውል በመግባት ምርቱን አምርተው ለገበያ ማቅረብ እንደሚችሉ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም