በሲዳማ ክልል በአፈርና ውሃ ጥበቃ ልማት የተገኘውን ውጤት ለማጠናከር ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል በአፈርና ውሃ ጥበቃ ልማት የተገኘውን ውጤት ለማጠናከር ይሰራል
ሀዋሳ ፤ጥር 19/2017 (ኢዜአ):-በሲዳማ ክልል ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ልማት ስራ የተገኘውን የምርትና ምርታማነት መሻሻል ውጤቶችን ለማጠናከር በተቀናጀ መንገድ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።
በክልሉ የ2017 ዓ.ም የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ “የአፈር ሀብታችን ለብልጽግናችን” በሚል መሪ ሀሳብ በቦርቻ ወረዳ አልዳዳ ደላ ቀበሌ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት የክልሉ መንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ አስፋው ጎኖሶ እንዳሉት፤ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚከሰቱ ችግሮች ለመከላከልና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ወሳኝ ነው።
በክልሉ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ስራዎች ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ማድረጉን አንስተው፤ ይህን ለማጠናከርና የምግብ ዋስትናን ጥረት ለማሳካት ታስቦ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ በበኩላቸው፤ በክልሉ ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ ከፍተኛ ለውጥ ማስመዝገቡን ተናግረዋል።
የደን ሽፋን እንዲጨምር የአፈር ለምነትንና የውሃ አቅምን እንዲያድግ እንዲሁም ለእንስሳት መኖ የሚሆን ሳር ማግኘት መቻሉን ለአብነት አንስተዋል።
ይህም በክልሉ ሁለንተናዊ የሆነ የምርትና ምርታማነት መጨመር ጉልህ ሚና እየተጫወተ በመሆኑ ልምዶችን እየወሰድን የማጠናከር ስራ ይሰራል ብለዋል።
በተያዘው ዓመት በ678 ንዑስ ተፋሰሶች ከ136 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት እንደሚለማ የቢሮው ምክትል ኃላፊና የተፈጥሮ ሀብትና መሬት አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፍቅረ ኢየሱስ አሸናፊ ገልጸዋል ።
በተለይም ውሃን ማቆር የሚያስችሉ ተግባራት ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው ሲሆን የሀዋሳ ሀይቅን ጨምሮ ሌሎች ውሃማ አካላት ከጎርፍና ደለል መከላከልን ታሳቢ ያደረገ የስነ-አካላዊ ስራ እንደሚከናወንም አንስተዋል።
የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው ለሚቀጥሉት 30 ቀናት እንደሚተገበርም ተናግረዋል።
ተዳፋታማ በሆነው የቦርቻ ወረዳ የአደላላ ደላ ቀበሌ በጎርፍ እየታጠበ መሬቱ ከምርት ወጥቶ እንደነበር ያስታወሱት ከልማቱ ተሳታፊዎች መካከል አርሶ አደር ኢሳያስ ባገ አሁን ለውጥ መኖሩን ገልጸዋል።
''የተፋሰስ ስራን አትኩረን በመስራታቸው ዛሬ ለእርሻ መሬትና ለከብት ሳር ማግኘት ችለናል።'' ያሉት አርሶ አደሩ ውጤቱን ለማስቀጠልም ከሌሎች ጋር በመሆን እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።
ወይዘሮ አሽለ ስና በበኩላቸው ከዚህ ቀደም አካባቢው እጅግ የተጎዳና ምርት የማይሰጥ አየሩም ምቹ እንዳልነበረ አንስተው ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የተፋሰስ ስራ በአካባቢው ለውጥ መጥቷል ብለዋል።
"በመሆኑም ስራውን ልምድ አድርገን እየሰራን ነው ዘንድሮም ከሌሎች ጋር በመሆን ወሩን ሙሉ እንሰራለን ጥቅሙ የእኛ ስለሆነ አጠናክረን እንቀጥላለን" ብለዋል።