ለአካባቢ ብክለት መንስኤ በሆኑ ከ1 ሺህ 800 በላይ አገልግሎት ሰጭና አምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል

አዲስ አበባ፤ ጥር 19/2017(ኢዜአ)፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ለአካባቢ ብክለት መንስኤ የሆኑ ከ1 ሺህ 800 በላይ አገልግሎት ሰጭና አምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የ2017 ዓ.ም የመጀመሪያ ስድስት ወራት የሥራ አፈፃፀም ገምግሟል፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዲዳ ድሪባ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ለአካባቢ  ጥበቃ እና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ትኩረት በመስጠት የ10 እና 5 ዓመት ስትራቴጂያዊ እቅዶች ተዘጋጅተው ወደ ስራ ተገብቷል፡፡


 

በመዲናዋ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ባለፉት ስድስት ወራት ለ12 አልሚዎች ፈቃድ እንዲሁም ለስድስት ተቋማት ደግሞ እድሳት ተደርጓል ብለዋል፡፡

በዚህም 2 ሚልየን 3 መቶ ሺህ ሜትር ኪዩብ ድንጋይና የድንጋይ ውጤቶች ለመዲናዋ የመሰረተ ልማት ግንባታ በማቅረብ ከ19 ሚሊዬን 762 ሺህ ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል ብለዋል፡፡

ባለስልጣኑ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል የተሻሻሉ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃ ለሚያቀርቡ 65 አምራች ማህበራት የአማራጭ ኢነርጂ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ድጋፍና ክትትል ማድረጉን አንስተዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ በአካባቢ ጥበቃ ላይ በቂ ግንዛቤ ለመፍጠር ለ 132 ሺህ ዜጎች ሥልጠና መሰጠቱን ጠቅሰው፤ የብክለት ይወገድልኝ ጥያቄ ላቀረቡ 923 ሰዎች ምላሽ ተሰጥቷል ብለዋል፡፡

በመዲናዋ የብክለት ምንጭ በሆኑ 8 ሺህ 772 አገልግሎት ሰጪ እና አምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ ክትትል መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በዚህም አካባቢን በተደጋጋሚ የሚበክሉ 1 ሺህ 801 ተቋማት ላይ ማሸግን ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸውንም ተናግረዋል።

እርምጃ የተወሰደባቸው ተቋማት የቆዳ፣ የብረታ ብረት እና የፕላስቲክ ፋብሪካዎች እንዲሁም ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች፣  ሆቴሎች መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ከድምጽ ብክለት ጋር በተያያዘም 50 የሚሆኑ የምሽት ቤቶች መታሸጋቸውን ገልጸው፤ በቀጣይ ማስተካከያ ካላደረጉ የንግድ ፈቃድ እስከ መሰረዝ የሚያደርስ ቅጣት ይጠብቃቸዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም