የመንግሥት አገልግሎትን የሚያዘምኑ ከ800 በላይ የዲጂታል ስርዓቶች ለምተዋል - ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥር 19/2017(ኢዜአ)፡- የመንግሥት አገልግሎትን በማዘመን ቀልጣፋና ተደራሽ ማድረግ የሚያስችሉ ከ800 በላይ የዲጂታል ስርዓቶች ለምተው ወደ ሥራ መግባታቸውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ገለጹ።

ከለውጡ ማግስት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በ2012 ዓ.ም ጸድቆ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) እንደገለጹት፥ የስትራቴጂው አምስት ዓመታት ትግበራ ጉልህ ውጤቶች የተገኙበት ነው።

መንግሥትና የግሉ ዘርፍ ለዲጂታል ስርዓተ ምህዳር ግንባታ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ በማድረግ በርካታ ስራዎች ማከናወናቸውን ገልጸዋል።

የዜጎች የዲጂታል እውቀትና ክህሎት መጎልበቱ፣ በርካታ መሰረተ ልማት መገንባቱ፣ የኔትወርክ ትስስር መሻሻሉ፣ የኢንተርኔት ተደራሽነትና የዲጂታል ፋይናንስ ስርዓት ማደጉ ከስኬቶች መካከል ናቸው ብለዋል።

ለአብነትም በቴሌ ብር የክፍያ ስርዓት ከ3 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር መፈጸሙን ጠቅሰዋል።


 

የስትራቴጂው አንዱ ዋነኛ ትኩረት የመንግሥት አገልግሎቶችን ቀልጣፋ፣ ዘመናዊና ፍትሐዊ ማድረግ እንደሆነም ሚኒስትሩ አንስተዋል።

በተለይም እያንዳንዱ አገልግሎት ከኋላ ቀር፣ ለሙስና ከሚያጋልጥና ግልፅ ካልሆነ ሂደት እንዲላቀቅና ወደ ዲጂታል እንዲሸጋገር በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት የትግበራ ጊዜም በርካታ አገልግሎቶች ወደ ኦንላይን ስርዓት መግባታቸውን ነው ያነሱት።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርም የመንግሥት አገልግሎትን የሚያዘምኑ ግልፅና ፈጣን የአገልግሎት ስርዓትን የሚፈጥሩ ከ800 በላይ ስርዓቶችን አልምቶ ወደ ስራ ማስገባቱን ጠቅሰዋል።

ስርዓቶቹ የተገልጋዮችን ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበት የሚቆጥቡ የመሆናቸውን ያህል፥ የተናበቡ፣ ብክነትን የማይፈጥሩና ለአጠቃቀም ምቹ እንዲሆኑ በየጊዜው መፈተሽ ቀጣይ የትኩረት ማዕከል ነው ብለዋል።


 

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግሥት ሀሚድ፥ የዲጂታል ሽግግር ጉዞው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የማበልጸግና የሳይበር ግንዛቤን በማሳደግ ረገድ አበረታች ውጤት ማምጣቱን አንስተዋል።

ሆኖም በሰው ኃይል ዝግጅት ማነስ፣ በተበታተነ መልኩ መስራት እና የዲጂታል ስርዓትን ደህንነት ሳያረጋግጡ የመጠቀም ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቅሰው መስተካከል አለባቸው ብለዋል።

የዲጂታል ትራንስፎርሜሽኑ የሳይበር መከላከል ስራን ለማጠናከር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አንስተው፥ ሆኖም የራሱ ስጋቶች እንዳሉት ጠቁመዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የዲጂታል ዕድገት የሚያመጣቸውን የሳይበር ደህንነት ስጋት ለመከላከል 24 ሰዓት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፥ ተቋማትም በራሳቸው ዝግጁ መሆን አለባቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም