የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 17ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 17ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ጥር 20/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 17ኛ ሳምንት መርሃ ግብር የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ።
በመጀመሪያ ጨዋታ መቀሌ 70 እንደርታ እና አርባምንጭ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
መቀሌ 70 እንደርታ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች በሶስቱ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ አቻ በመውጣት አራት ግቦችን ሲያስቆጥር ምንም ግብ አላስተናገደም።
ቡድኑ በ21 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
አርባምንጭ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት ተከታታይ አምስት ጨዋታዎች አራት ጊዜ ድል ሲቀናው አንድ ጊዜ ተሸንፏል።
ቡድኑ በጨዋታዎቹ ስድስት ግቦችን ሲያስቆጥር ሁለት ግቦች ተቆጥረውበት በ22 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በሌላኛው የ17ኛ ሳምንት መርሃ ግብር አዳማ ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።
አዳማ ከተማ በሊጉ ካከናወናቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች መካከል ያሸነፈው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን ሶስት ጊዜ ሲሸንፍ አንድ ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።
በአምስቱ ጨዋታዎች ስድስት ግቦችን ሲያስቆጥር ስምንት ግቦችን አስተናግዶ በ15 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ላይ ይገኛል።
የአምናው የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ በሊጉ ካደረጋቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ አንድ ጊዜ ተሸንፎ ሶስት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።
በጨዋታዎቹ ሶስት ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያገናኝ በተመሳሳይ ሶስት ግቦችን አስተናግዶ በ15 ነጥብ ተጋጣሚውን በግብ ክፍያ በልጦ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
የ17ኛ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ ጥር 23 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።
ሲዳማ ቡና እና ስሑል ሽሬ የሳምንቱ አራፊ ቡድኖች ናቸው።
ኢትዮጵያ መድን በ29 ነጥብ ሊጉን ሲመራ መቻል በ27፣ ሀዲያ ሆሳዕና በ26 እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በ25 ነጥብ ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
አዳማ ከተማ፣ ስሑል ሽሬ፣ ሃዋሳ ከተማ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከ15ኛ እስከ 18ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።
የድሬዳዋ ከተማው መሐመድ ኑር ናስር፣ የኢትዮጵያ ቡናው አንተነህ ተፈራ፣ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ፍጹም ጥላሁን፣ ሽመልስ በቀለ ከመቻል፣ የመቀሌ 70 እንደርታው ያሬድ ብርሃኑ፣ የወላይታ ድቻው ያሬድ ዳርዛ እና የአርባምንጭ ከተማው አህመድ ሁሴን በተመሳሳይ ስድስት ግቦች የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት በጋራ ይመራሉ።`