የመሬት ናዳ ዳግም እንዳይከሰት በተፋሰስ ልማቱ በንቃት እንሳተፋለን - የኬንቾ ወይዜ ቀበሌ ነዋሪዎች

ሳውላ፤ ጥር 20/2017(ኢዜአ)፡- በአካባቢያቸው የመሬት ናዳ ዳግም እንዳይከሰትና የተጎዳ መሬት መልሶ እንዲያገግም በተፋሰስ ልማቱ በንቃት በመሳተፍ የበኩላቸውን እንደሚወጡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ በገዜ ጎፋ ወረዳ የኬንቾ ወይዜ ቀበሌ ነዋሪዎች ገለጹ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የዘንድሮው የበጋ ተፋሰስ ልማት በገዜ ጎፋ ወረዳ በይፋ ባስጀመረበት ወቅት ኢዜአ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በገዜ ጎፋ ወረዳ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ/ም የተከሰተውን ዓይነት የተፈጥሮ አደጋ እንዳይደገም ለማድረግ አካባቢያቸውን ለመንከባከብ በተፋሰስ ልማት ስራዎች በንቃት እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።

የኬንቾ ወይዜ ቀበሌ አካባቢ ጥበቃ አርሶ አደሮች ማህበር ሰብሳቢ አቶ ተክሌ ባዝዴ እንደገለጹት፤ የአካባቢውን የተፈጥሮ ሃብት በመንከባከብ አደጋን መቀነስ ይቻላል።

በአካባቢው ላይ የተፋሰስ ልማት ስራ መስራት ስለሚጠቅም ከሚመለከተው የወረዳው አካል ጋር በመሆን ይህን ቦታ ለማልማት የልኬት ስራ ሰርተናል ብለዋል። 

በስፍራው ሊከሰት የሚችለውን የመሬት ናዳ እና ጎርፍ ለመከላከል የአካባቢው ማህበረሰብ ተስማምቶ ወደ ስራ መግባቱንም ተናግረዋል።


 

ሌላዋ የማህበሩ አባል ወይዘሮ መሰለች አበበ በበኩላቸው፤ ያለንበት ስፍራ ላይ ያለውን የተጎዳ መሬት በማልማት አፈሩ እንዳይሸረሸር፣ ውሀውም እዚሁ እንዲቆይና ናዳ እንዳይከሰት ለመከላከል ለስራ ወጥተናል ብለዋል።

ቀድሞ ይህ ቦታ ለምቶ ቢሆን ኖሮ አደጋው አይከሰትም ብየ አስባለሁ ያሉት አስተያየት ሰጪዋ፤ አሁን አካባቢውን በማልማት ችግሩን መከላከል እንደሚቻል መገንዘባቸውን ተናግረዋል።


 

ከማህበሩ አባላት መካከል ወጣት ስምኦን ስሜ እንደገለጸው፤ በተፋሰስ ልማቱ ዙሪያ የተለያዩ እጽዋትንና የእንስሳት መኖ በማልማት ተጠቃሚ ለመሆን እየሰሩ ይገኛሉ።

የፋሰስ ልማቱ መሰራቱ መሬቱ እንዳይሸራተት ያደርጋል የሚል እምነት እንዳለው ገልጿል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተያዘው ዓመት 421 ሺህ 378 ሄክታር የተጎዳ መሬት ላይ ለአንድ ወር የሚቆይ የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ስራ ጥር 15 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ መጀመሩን መዘገባችን ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም