በሁለቱ ዞኖች ከ183 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት ስራ ይከናወናል

ሮቤ፤ ጥር 21/2017(ኢዜአ)፦ በባሌ እና ምስራቅ ባሌ ዞኖች ዘንድሮ በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ከ183 ሺህ ሔክታር መሬት በላይ በሥነ-አካላዊ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ እንደሚከናወን የየዞኖቹ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጹ። 

የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራው በምሥራቅ ባሌ ዞን የተጀመረ ሲሆን በባሌ ዞን ደግሞ ስራውን ለመጀመር ዝግጅት መጠናቀቁ ተመልክቷል።

የምሥራቅ ባሌ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘላለም አለማየሁ እንዳሉት የዘንድሮው የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት በዞኑ በተለዩ 155 ንዑስ ተፋሰሶችን መሰረት በማድረግ ከ77 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ የሚያካልል ነው።



በዞኑ ለአፈር መሸርሸርና ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ ተዳፋታማና ተራራማ አካባቢዎችን የማልማት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ ይከናወናል ብለዋል።

የባሌ ዞን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሰለሞን ዳዲ በዞኑ በዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ሥራ 105 ሺህ 800 ሄክታር መሬትን መሰረት በማድረግ የተለያዩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች እንደሚከናወኑም አመልክተዋል።

በዞኑ በዋና ዋና የአፈርና ውኃ መጠበቂያ ስትራክቸሮች፤ እርከን እንዲሁም የተጎዳ መሬትን ከሰውና እንስሳት ንክኪ ነፃ አድርጎ የማልማት ሥራ ለማከናወን መታቀዱን አብራርተዋል።

የተፈጥሮ ሀብትን የመጠበቅ፤ የማልማትና የመጠቀም ጉዳይ ትውልድን የማስቀጠል አጀንዳ መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም የዞኑ ህዝብ በስፋት እንዲሳተፍ ቅስቀሳ እየተደረገ መሆኑንም እንዲሁ።




የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም