በፕሪሚየር ሊጉ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ 

አዲስ አበባ፤ጥር 21/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ17ኛ ሳምንት መርሃ ግብር የሁለተኛ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ወላይታ ድቻ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ወላይታ ድቻ በሊጉ ካደረጋቸው ያለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 

በአምስቱ ጨዋታዎች ስድስት ጎሎችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ ስድስት ግቦች አስተናግዷል። ቡድኑ በ20 ነጥብ 8ኛ ደረጃን ይዟል። 

ተጋጣሚው ቅዱስ ጊዮርጊስ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች  አራት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።

በጨዋታዎቹ ስምንት ግቦችን ሲያስቆጥር ሶስት ግቦች ተቆጥረውበታል። 

ቡድኑ በ25 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 

በሌላኛው የ17ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ቡና ከባህር ዳር ከተማ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች በሁለቱ ድል ሲቀናው አንድ ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 

በጨዋታዎቹ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር አንድ ግብ አስተናግዷል። ቡድኑ በ19 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል።

ባህር ዳር ከተማ ካለፉት አምስት ተከታታይ የሊጉ ጨዋታዎች መካከል ድል የቀናው በአንዱ ነው። አንድ ጊዜ ሲሸነፍ ሶስት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። 

በጨዋታዎቹ ሶስት ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ በተመሳሳይ ሶስት ጎሎች ተቆጥረውበታል። ባህር ዳር ከተማ በ23 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በተያያዘ ዜና ትናንት በተደረጉ የ17ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዳማ ከተማን 2 ለ 0 ሲያሸንፍ መቀሌ 70 እንደርታ እና አርባምንጭ ከተማ ሁለት አቻ ተለያይተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም