በክልሉ በስድስት ወራት ውስጥ ከ30 ሺህ በላይ ዜጎች የኮደርስ ስልጠና ወስደዋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በስድስት ወራት ውስጥ ከ30 ሺህ በላይ ዜጎች የኮደርስ ስልጠና ወስደዋል
ቡታጅራ፤ ጥር 21/2017 ዓ/ም (ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት 30 ሺህ 955 ዜጎች በኮደርስ ስልጠና መሳተፋቸውን የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ አስታወቀ፡፡
ቢሮው የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት እቅድ አፈፃፀምና በቀጣይ ወራት የትኩረት አቅጣጫ ላይ የተዘጋጀ የምክክር መድረክ በቡታጅራ ከተማ እያካሄደ ነው፡፡
የቢሮው ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ በዚህ ወቅት እንዳሉት በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት 30 ሺህ 955 ዜጎች በኮደርስ ስልጠና ተሳትፈዋል፡፡
ከዚህ ውስጥ ከ15 ሺህ በላይ የሚሆኑት ስርተፊኬት መውሰዳቸውን ገልጸው ቀሪዎቹ ደግሞ በስልጠና ሂደት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
በመንግሥት ተቋማት የሚገኙ ሰልጣኞች ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን ሌሎች ወጣቶችም ከተለያዩ ኩባንያዎች ጋር ተቀናጅተው እንዲሰሩ መመቻቸቱን ገልጸዋል፡፡
በክልሉ በበጀት ዓመቱ 49 ሺህ 571 የሚሆኑ ዜጎች የኮደርስ ስልጠና እንዲወስዱ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የቢሮው ከፍተኛ አመራር አባላት፤ የዞንና የልዩ ወረዳ የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ናቸው፡፡