በክልሎች ትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፉን ለማዘመን ቴክኖሎጂ መር አሰራሮች ተዘርግተዋል

አዳማ፤ ጥር 21/2017 (ኢዜአ)፦ የትራንስፖርት አገልግሎትን ዘርፉን ለማዘመን በቴክኖሎጂ የተደገፉ አሰራሮች መዘርጋታቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የክልልና የከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮዎች ገለጹ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ የኦሮሚያ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ሀላፊዎች የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር እየዘረጉ ነው።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መሀመድ ኑርዬ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት ስድስት ወራት የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማሳለጥና ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል።

በህዝብ መናኽሪያዎች ተገልጋዩን የሚያንገላቱና ከታሪፍ በላይ ክፍያን ለማስወገድ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር እየተተገበረ መሆኑን ገልጸዋል።

በ11 መናኸሪያዎች የኤሌክትሮኒክ ትኬት(ኢ-ትኬት) አገልግሎት መተግበሩን ገልጸው፤ ይህን በሌሎች መናኸሪያዎች ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የመንጃ ፍቃድና የአሽከርካሪዎች ስልጠና አገልግሎቱን ከኪራይ ሰብሳቢነት የጸዳ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች እንደላ ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ትራንስፖርት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ቸርነት በበኩላቸው አገልግሎቱን ለማዘመን በክፍያ፣ በተሽከርካሪ ስምሪት፣ በመንጃ ፍቃድ እድሳት፣ በተሽከርካሪ የቴክኒክ ፍተሻና የቦሎ አሰጣጥ የአንድ መስኮት አገልግሎት መጀመሩን አመልክተዋል።

የመንጃ ፍቃድን ህጋዊነት ለመቆጣጠርም የ'ኦን ላይን' ምዝገባ ቋት መዘጋጀቱን ገልጸው፤ የአሸከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማትንና የቦሎ አገልግሎትን በሲሲቲቪ ካሜራ በመከታተል የሥነ ምግባር ችግሮች ቁጥጥር እየተደረገ ስለመሆኑ አስረድተዋል።

በክልሉ በ290 መናኸሪያዎች ላይ የኢ-ትኬት አገልግሎት በማስጀመር ህብረተሰቡን ከእንግልትና አላስፈላጊ ወጪ መታደግ ተችሏ ብለዋል።

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ወርቁ ደስታ፤ በመዲናዋ የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማሳለጥ በተለይ የከተማ አውቶቢስ ሪፎርም ማድረጉን ጠቅሰዋል።

የትራንስፖርት ምልልሱን በመጨመር ህብረተሰቡ በፍጥነት አገልግሎት ማግኘት የሚችልበት አሰራር መዘርጋቱን አስታውቀዋል።

የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ብቃትን ለማሳደግም በቴክኖሎጂ የታገዘ ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የስድስት ወር የዕቅድ አፈፈፃፀም ግምገማ ተጠሪ ተቋማት፣ የክልልና ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮዎች እና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት መድረክ በቅርቡ በአዳማ መካሄዱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም