በብሔራዊ ፓርኩ የሚፈፀም ሕገ ወጥ አደንና ሰፈራን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በብሔራዊ ፓርኩ የሚፈፀም ሕገ ወጥ አደንና ሰፈራን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው
ሳላማጎ፤ ጥር 21/2017 (ኢዜአ)፦ በማጎ ብሔራዊ ፓርክ የሚፈፀም ሕገ ወጥ አደንና ሰፈራን ለመከላከል ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የፓርኩ አስተዳደር አስታወቀ።
ከአዲስ አበባ በ790 ኪሎ ሜትር ርቀት በውብ መልክዓ ምድርና በጥቅጥቅ ደኖች ማራኪ ገጽታ የተላበሰው የማጎ ብሔራዊ ፓርክ በደቡብ ክልል በታችኛው ኦሞ ሸለቆ ይገኛል።
በ1970 ዎቹ ገደማ በፓርክነት የተቋቋመውና የበርካታ ብዝሃ ሕይወት መገኛ የሆነው ፓርኩ፤ ከ80 በላይ አጥቢ፣ ከ250 በላይ የአዕዋፍ እና 14 ዓይነት የዓሣ ዝሪያዎች አሉት።
ዝሆን፣ የሜዳ አህያ፣ አንበሳ፣ ጎሽ፣ አምባራይሌ፣ አቦሸማኔ፣ ተኩላና የሌሎች አጥቢ የዱር እንስሳት የያዘ የመስህብ ስፍራ ነው።
የማጎ ብሔራዊ ፓርክ አስተዳዳሪ አቶ አርቦር ሌለ ለኢዜአ እንደገለጹት ፓርኩ በሕገ ወጥ ሰፈራ፣ በእርሻ መሬትና በሌሎች ምክንያቶች ፓርኩ ጉዳት እያስተናገደ ነው።
በዚህም የፓርኩ ይዞታ ከ2 ሺህ 142 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ስፋት ወደ 1 ሺህ 942 ዝቅ ማለቱን ጠቁመዋል።
በአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ በኩል የሚፈጽምን ሕገ ወጥ አደን ለማስቆም በሚንቀሳቀሱ የፓርክ ስካውት አባላት ላይ ጥቃት እንደሚሰነዘር ገልጸዋል።
በመሆኑም የፓርኩን ደህንነትና ብዝሀ ሀብት ለማስጠብቅ ህብረተሰቡንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በመጡ መሻሻሎች ወደ ጎረቤት አገራት የተሰደዱ የዱር እንስሳትም መመለስ መጀመራቸውን ነው ያነሱት።
የፓርኩ የስካውት አባል አቶ ሻዳ ቡኬ በበኩላቸው፣ ሕገ ወጥ አደንን ለመከላከል በሚደረግ ጥረት በርካታ ስካውቶች የጥቃት ሰለባ እንደሚሆኑ ገልፀው፤ ድርጊቱን ለማስቆም የተጀመረው ጥረት ለውጥ እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።
ፓርኩን በዘላቂነት ለመጠበቅና ለሚፈለገው ቱሪስት መስህብነት ለማዋል ለፓርኩ ትኩረት መስጠት ይገባዋል ነው ያሉት።
በበናፀማይ ወረዳ ጎልዲያ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ከበደ ቦጋለ፤ እንደ ጀግንነት የሚያስቆጥረው ግዙፍ የዱር እንስሳትን አድኖ የመግደል የአካባቢው ጎጂ ባህል እንዲቀረፍ በተደረገው ጥረት ጥሩ ለውጦች እየታዩ ነው ብለዋል።
በአሪ ዞን የአልጋ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ዘውዱ አንክሲ በበኩላቸው የእርሻ ማሳ ለማስፋፋት ወደ ፓርኩ ይዞታ በህገ ወጥነት የመስፈር ሁኔታ እንደሚስተዋል ገልፀው፤ ይህን ሕገ ወጥ ድርጊት ለመከላከል የፀጥታ አካላት ጋር ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።