በአማራ ክልል የኮደርስ ስልጠና ፕሮጀክትን ማሳካት የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ - የክልሉ ስራና ስልጠና ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የኮደርስ ስልጠና ፕሮጀክትን ማሳካት የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ - የክልሉ ስራና ስልጠና ቢሮ
ጎንደር፤ ጥር 21/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል እየተከናወነ የሚገኘው የኢትዮ ኮደርስ የስልጠና ፕሮጀክትን ማሳካት የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን የአማራ ክልል ስራና ስልጠና ቢሮ ገለጸ።
በክልሉ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና መርሃ ግብር የ6 ወራት የስራ አፈጻጸም የግምገማ መድረክ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ተካሂዷል፡፡
በጎንደር ከተማ በተካሄደው በዚሁ መድረክ የተገኙት የክልሉ ስራና ስልጠና ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ አማረ አለሙ እንደተናገሩት፤ ፕሮጀክቱ ወጣቶች የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎትና እውቀት በማዳበር ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን ከፍ የሚያደርግ ነው፡፡
ይህም እውቀትና ክህሎትን በማስታጠቅና በማብቃት ዘመኑን የዋጀ ትውልድ መገንባት ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት ዜጎችን የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አመልክተው፤ ከ205 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶችና ለሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ፈጠራ ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል፡፡
ስልጠናውን የሚከታተሉ ሰልጣኞች 45ሺህ መድረሳቸውን ጠቁመው፤ ከ23ሺህ በላይ የሚሆኑት ስልጠናቸውን አጠናቀው ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው ሰርቲፊኬት መቀበለቻውን አስረድተዋል።
ስልጠናው በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ በዳታ ሳይንስና በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎትና ብቃት በማሳደግ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን የሚያሳድግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ተደራሽ ለማድረግ ለተያዘው ዕቅድ ስኬታማነት አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በየደረጃው ያለ የአመራር አባል ተልዕኮዎችን ተቀብሎ በመፈጸም ለፕሮጀክቱ መሳካት እንዲረባረብ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ፕሮጀክቱን የሚከታተልና የሚደግፍ አንድ ዐቢይ እና የቴክኒክ ከሚቴዎች ተዋቅረው ስልጠናውን ለማሳካት እየሰራ ነው ያሉት የዞኑ አስተዳደር ተወካይ አቶ ዳንኤል ወርቁ ናቸው፡፡
ኢትዮ ኮደርስ የወጣቶችን የዲጂታል ቴክኖሎጂ የአስተሳሰብ አድማስ ማስፋትና ማጎልበት የሚያስችል አለም አቀፍ ኢኒሼቲቭ መሆኑን ጠቁመው፤ የዲጂታል ክህሎት ስልጠና መርሃ ግብሩ እንዲሳካ የአመራር አባላት በትኩረት እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ስራና ስልጠና መምሪያ ሃላፊ አቶ እዮብ አግማስ በበኩላቸው፤ በዞኑ የስልጠና ማዕከላት ተቋቁመው በ92 የስልጠና አመቻቾች መርሃ ግብሩ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ የስልጠና ዕድሉ ተጠቃሚ ለማድረግ ከታቀደው ውስጥ እስካሁን 5ሺህ 280 ስልጠና መውሰዳቸውን አስታውቀዋል፡፡
በመድረኩ በየደረጃው ያሉ አመራር አባላት በተገኙበት የስድስት ወራት የአፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ተገምግሟል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት በኢትዮጵያና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መንግስታት ትብብር የ"አምስት ሚሊዮን ኮደርስ" መርሃ ግብር በመላ ሀገሪቱ እየተተገበረ ይገኛል፡፡