ኢትዮ ቴሌኮም 5 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎችን ለዲጂታል መታወቂያ(ፋይዳ) መዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮ ቴሌኮም 5 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎችን ለዲጂታል መታወቂያ(ፋይዳ) መዝግቧል
አዲስ አበባ፤ ጥር 21/2017(ኢዜአ)፡-ኢትዮ ቴሌኮም እስካሁን 5 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎችን ለዲጂታል መታወቂያ(ፋይዳ) መመዝገቡን አስታወቀ።
ከ427 ሺህ በላይ የመታወቂያ ካርዶች ታትመው ለህብረተሰቡ ተደራሽ መሆናቸውንም ገልጿል።
የኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ ከስተመር ኤክስፒሪያንስና ኳሊቲ ኦፊሰር ሰለሞን አበራ እንዳሉት ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እየሰራ ይገኛል፡፡
በዚህም ከብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር ስምምነት በማድረግ በ275 ከተሞች የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ እየተካሄደ ነው ብለዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ ለዲጂታል መታወቂያ ከተመዘገቡ 11 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች ውስጥ ኢትዮ ቴሌኮም 5 ነጥብ 5 ሚሊየኑን መመዝገቡን ተናግረዋል።
በዓመት እስከ 48 ሚሊየን መታወቂያዎችን ማተም የሚችሉ ማሽኖች በማስገባት የህትመት ስራን እያፋጠነ ነው ያሉት አቶ ሰለሞን አበራ፥ መታወቂያው ለ10 ዓመት ማገልገል እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
እስካሁን ባለው ሂደት በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ ሃዋሳ፣ ነቀምትና ወላይታ ሶዶ ከተሞች መታወቂያ እየታተመ ለህብረተሰቡ ተደራሽ መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም የመታወቂያ ህትመት አገልግሎቱን እስከ የካቲት ወር አጋማሽ ድረስ በሁሉም አካባቢዎች ለማስፋት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የካርድ ህትመት ከተጀመረ ከሁለት ወር በላይ ያስቆጠረ ሲሆን፥ 427 ሺህ የመታወቂያ ካርዶች ታትመው ለህብረተሰቡ እንዲደርሱ መደረጉንም ነው የገለጹት።
በአዲስ አበባ 63 የካርድ መረከቢያ ቦታዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፥ በቴሌ ብር ክፍያ በመፈፀም የዲጂታል መታወቂያ ካርዱን መውሰድ እንደሚችሉም ተናግረዋል።
በኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል መታወቂያ ካርዳቸውን ለመውሰድ ከመጡ ተገልጋዮች መካከል ጌታቸው ዓለሙ እና ባንቴ ጌትነት በበኩላቸው፥ ከምዝገባ ጀምሮ ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።