በፕሪሚየር ሊጉ ኢትዮጵያ ቡና ባህር ዳር ከተማን አሸነፈ - ኢዜአ አማርኛ
በፕሪሚየር ሊጉ ኢትዮጵያ ቡና ባህር ዳር ከተማን አሸነፈ
አዲስ አበባ ፤ ጥር 21/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ17ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ቡና ባህር ዳር ከተማን 3 ለ 1 አሸንፏል።
ማምሻውን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ጋናዊው ኮንኮኒ ሃፊዝ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር አንተነህ ተፈራ ቀሪዋን ጎል ለኢትዮጵያ ቡና ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ሙጂብ ቃሲም ለባህር ዳር ከተማ ብቸኛዋን ግብ ከመረብ ጋር አገናኝቷል።
ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና በ22 ነጥብ ደረጃውን ከ10ኛ ወደ 7ኛ ከፍ አድርጓል። በውድድር ዓመቱም ስድስተኛ ድሉን አስመዝግቧል።
በሊጉ አምስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ባህር ዳር ከተማ በበኩሉ በ23 ነጥብ 5ኛ ደረጃን ይዟል።
ቀን ላይ በተደረገ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወላይታ ድቻን 2 ለ 0 አሸንፏል።