በሊጉ የሶስተኛ ቀን ውሎ ሁለት ወሳኝ መርሃ ግብሮች ይደረጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሊጉ የሶስተኛ ቀን ውሎ ሁለት ወሳኝ መርሃ ግብሮች ይደረጋሉ
አዲስ አበባ፤ጥር 22/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ17ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ አንድ ጨዋታ አቻ ወጥቷል።
በአምስቱ ጨዋታዎች ሶስት ጎሎችን ሲያገባ በተመሳሳይ አራት ግቦች አስተናግዷል። ቡድኑ በ18 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ለይ ይገኛል።
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች መካል በአንዱ ድል ሲቀናው ሶስት ጊዜ ተሸንፏል። አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።
በጨዋታዎቹ ሁለት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ሰባት ግቦች ተቆጥረውበት በአምስት ነጥብ የመጨረሻውን 18ኛ ደረጃ ይዟል።
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ16ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ሀዲያ ሆሳዕናን 1 ለ 0 በማሸነፍ በሊጉ የመጀመሪያ ድሉን ማስመዝገቡ የሚታወስ ነው።
በሌላኛው የ17ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ሃዋሳ ከተማ ከመቻል ከተማ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሃዋሳ ከተማ ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች አላሸነፈም። ሁለት ጊዜ ሲሸነፍ በሶስቱ ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።
በጨዋታዎቹ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር አምስት ጎሎች አስተናግዷል። ቡድኑ በ12 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ተጋጣሚው መቻል በበኩሉ ካለፉት አምስት ተከታታይ የሊጉ ጨዋታዎች መካከል ያሸነፍ አንድ ጊዜ ብቻ ነው። አንድ ጊዜ ሲሸነፍ ሶስት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።
በጨዋታዎቹ አራት ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ አራት ጎሎች ተቆጥረውበታል። መቻል በ27 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
መቻል የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ የሊጉን መሪነት በጊዜያዊነት ከኢትዮጵያ መድን ይረከባል።
በተያያዘ ዜና ትናንት በተደረጉ የ17ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ ወላይታ ድቻን 2 ለ 0 እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና ባህር ዳር ከተማን 3 ለ 1 አሸንፈዋል።