በአካባቢያችን የተከናወነ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የተጎዳ መሬት እንዲያገግም አስችሏል-የዞኑ አርሶ አደሮች

ጂንካ ፤ ጥር 22/2017 (ኢዜአ)፡-በአካባቢያቸው በተከናወነ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የተጎዳ መሬት አገግሞ ምርት እየሰጠ መሆኑን የአሪ ዞን አርሶ አደሮች ገለፁ።

በአሪ ዞን ባሉ ሁሉም የወረዳና የከተማ አስተዳደር መዋቅሮች የ2017 ዓ.ም የተፋሰስ ልማት ንቅናቄ በስፋት እየተከናወነ ነው።

በዞኑ የሰሜን አሪ ወረዳ የሻማ ቡልቀት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሀሳቡ ዓለማ ባለፉት ሦስት ዓመታት በአካባቢው የተፋሰስ ልማት ሥራ በስፋት መከናወኑን ተናግረዋል።


 

ሁሉም በንቃት በመሳተፍ በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች የተጎዱና ምርት መስጠት የማይችሉ የእርሻ ማሳዎች አገግመው ምርት መስጠት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

አካባቢያቸው ተዳፋት በመሆኑ ከዚህ ቀደም የአፈር መንሸራተት እና የጎርፍ አደጋ ስጋት እንደነበረባቸው አስታውሰው፣ በተለይም ክረምት ሲመጣ የአደጋ ስጋቱ ከፍተኛ እንደነበር ተናግረዋል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት በአካባቢው በተፋሰስ ልማት በተሰሩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች የጎርፍና የአፈር መንሸራተት አደጋን መከላከል እንደተቻለም አመልክተዋል።

"የተፋሰስ ሥራው ከዚህ ቀደም በጎርፍ ይታጠብ የነበረን ለም አፈር አስቀርቷል" ያሉት ደግሞ በወረዳው የገሊላ ዙሪያ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሀብታሙ ባህሩ ናቸው።

ቀደም ሲል በአካባቢው የደን መመናመን፣ የምንጮች መድረቅና የእርሻ ማሳዎች ለምነት ማጣት ችግሮች እንደነበሩ አስታውሰዋል።

እንደ አርሶ አደር ሀብታሙ ገለጻ፣ ባለፉት ዓመታት በህብረተሰቡ ተሳትፎ በአካባቢው በተሰሩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች እነዚህ ችግሮች እየተፈቱ መጥተዋል።

የተፋሰስ ልማቱ ካስገኘላቸው ዘርፈ ብዙ ጥቅም አንጻር ዘንድሮውም ልማቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

የአሪ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ታፈሰ ተስፋዬ፤ ከዚህ ቀደም በዞኑ የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ባመጡት ተጨባጭ ውጤት ህብረተሰቡ ተጠቃሚ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ልማቱን አጠናክሮ ለማስቀጠልም በዘንድሮ ዓመት ህብረተሰቡን በማሳተፍ በ105 ንዑስ ተፋሰሶች ከ23 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የአፍርና ውሃ ልማትና ጥበቃ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

በተጨማሪም በዞኑ በሚገኙ አራት ወረዳዎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች በእያንዳንዳቸው አንድ ተራራ ለማልማት መታቀዱን አስታውቀዋል።

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም