በክልሉ ባለፉት አምስት ዓመታት የተከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራ የደን ሽፋኑን ከማሳደግ አንጻር ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል - የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ

አዳማ፤ ጥር 22/2017(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል ባለፉት አምስት ዓመታት የተከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራ የደን ሽፋኑን ከማሳደግ አንጻር ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ዘርፍ ምክትል ሃላፊ አቶ ኢሊያስ ከድር ለኢዜአ እንደገለጹት የተፈጥሮ ሀብትን በማልማት ለትውልድ ለማስተላፍ እየተሰራ ነው።

በተለይም ባለፉት አምስት ዓመታት የክልሉ የተፋሰስና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራዎች ለግብርናው ምርታማነትና ለአካበቢ ስነ-ምህዳር መጠበቅ ወሳኝ ሚና እያበረከቱ ይገኛሉ ብለዋል።

ይህም በመሆኑ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራው በክልሉ መንግስት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተመራ መሆኑንም አስረድተዋል።

በተፈጥሮ ሀብት ልማት በአምስት ዓመታት ውስጥ ከተተከሉት የተለያዩ ዝርያ ያላቸው ችግኞች የጽድቀት ምጣኔያቸው የተሻለ መሆኑንም ተናግረዋል።

ይህም የደን ሽፋኑን ቀደም ሲል ከነበረበት 17 በመቶ ወደ 27 ነጥብ 6 በመቶ ማሳደጉን ተናግረዋል።

የተፈጥሮ ሀብት ልማቱ የደረቁ ወንዞች፣ ጅረቶችና ሃይቆችን ከመመለስ ባለፈ በድርቅ ተጋላጭ የነበሩ የክልሉ አካባቢዎች በእንስሳት መኖ እንዲያከማቹ ማገዙን አስረድተዋል።

የተፋሰስ ልማቱ ምርታማነትን ከመጨመር ባለፈ በንብ ማነብ፣ በመኖ አቅርቦትና በተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ የስራ ፈጠራ እድልን እየፈጠረ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህ አመትም ለ60 ቀናት የተፋሰስ ልማት ስራን ለማካሄድ መታቀዱንና ህዝቡ ለዚሁ ስራ በጉልበቱና በእውቀቱ የሚያበረክተው አስተዋጽኦም በገንዘብ ሲተመን ትልቅ መሆኑን አክለዋል።

ዘንድሮ በ6 ሺህ 495 ተፋሰሶች ላይ በ3 ነጥብ 3 ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ እቀባ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

ከተያዘው የጥር ወር አጋማሽ ጀምሮ እየተከናወነ ያለው የተፋሰስ ልማቱ ስራ ሳይንስዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲከናወን አመራሩና ባለሙያዎች እገዛ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም