በክልሉ የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ አድርገዋል - ኢንጂነር ምትኩ በድሩ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ አድርገዋል - ኢንጂነር ምትኩ በድሩ(ዶ/ር)
ሺሾ-እንዴ፤ ጥር 22/2017(ኢዜአ)፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረጋቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የኢኮኖሚ አማካሪ ኢንጂነር ምትኩ በድሩ(ዶ/ር) ተናገሩ።
በክልሉ የ"አፈር ሀብታችን ለብልጽግናችን" በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው የዘንድሮው የበጋ ወቅት የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ በካፋ ዞን ሺሾ እንዴ ወረዳ ተጀምሯል።
መርሃ ግብሩን ዛሬ በይፋ ያስጀመሩት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የኢኮኖሚ አማካሪ ኢንጂነር ምትኩ በድሩ(ዶ/ር) በክልሉ የተፈጥሮ ሀብትን መጠበቅና መንከባከብ የቆየ ልምድ አለ።
ባለፉት ዓመታት ከ1 ሚሊዮን 745 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ በ1 ሺህ 64 ንዑስ ተፋሰሶች ላይ 185 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ማልማት መቻሉን ገልፀዋል።
በለሙ አካባቢዎችም ከ28ሺህ 700 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች በመደበኛና በፕሮጀክቶች ወደ ስራ ገብተው እየተጠቀሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለ45 ቀናት በሚቆየው በዚህ የተፋሰስ ልማት ያረጁ ቡናዎችን የመጎንደል፣ የጉድጓድ ዝግጅት፣ የእርከንና ሌሎች ሥነ አካላዊ ሥራዎች እንደሚከናወኑም ተመላክቷል።